የእስራኤል አክስዮን ነጋዴዎች ስለ ሐማስ ጥቃት ቀድመው ያውቁ ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
መስከረም 26/2016 ዓ.ም ሐማስ እስራኤል ላይ ሊያደርስ ያቀደውን ጥቃት የአክስዮን ድርሻ ነጋዴዎች ቀድመው ያውቁ ነበር መባሉን በተመለከተ እስራኤል ምርመራ እንደምታካሂድ አስታውቃለች።
አንድ አካዳሚያዊ ጥናት የአክስዮን ድርሻ ነጋዴዎች በጥቃቱ ምክንያት የእስራኤል ኢኮኖሚ ሊያጋጥመው የሚችለው ሁኔታ ላይ “በመቆመር” ትልቅ ትርፍ አግኝተዋል ሲል አመልክቷል።
አጥኚዎቹ በጥቃቱ ጊዜ የአክስዮን ድርሻ ነጋዴዎች ‘ፈጣን ሽያጮችን’ ሲያከናውኑ እንደነበር ጠቅሰዋል።
‘ፈጣን ሽያጭ’ ነጋዴዎች ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸው ቀድመው ከተረዱት የአክስዮን ድርሻቸውን፣ ቦንድ ወይም ሌላ የፋይናንስ አማራጭን ለገበያ በማቅርብ ገንዘብ ለማግኘት የሚሞክሩበት ዘዴ ነው።
ይህንንም የሚያደርጉት በዝቅተኛ ዋጋ ሲሆን፣ የገበያው ዋጋ መልሶ ከመረጋጋቱ በፊት መልሰው በርካሽ ዋጋ እንደሚገዙት ተስፋ በማድረግ ያከናውኑታል።
በኮሎምቢያ እና በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት አጥኚዎቹ “ጥቃቱ ከመፈጸሙ አንድ ቀን ቀድመው፣ የሚመጣውን ነገር አስቀድመው በመገመት የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ሲከናወን ነበር” ብለዋል።
ጨምረውም ‘ፈጣን ሽያጩ’ ከዚህ ቀደም ከነበረው የፋይናንስ ቀውስ፣ በአውሮፓውያኑ 2014 ከነበረው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት እና ከኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ወቅቶች በላቀ ሁኔታ ሲከናወን ነበር ብለዋል።
በቴላ አቪቭ ‘የስቶክ ገበያ’ በአስገራሚ ሁኔታ የእስራኤል ተቋማት የድርሻ ሽያጭ ጨምሮ ታይቷል።
በሌላ በኩል አጥኚዎቹ የእስራኤል የገበያ ድርሻ ሽያጭን የሚከታተል አንድ ተቋም ያልተለመደ ከፍተኛ የሽያጭ እንቅስቃሴ መመልከቱን ገልጸዋል።
ጥናቱ የእስራኤል የአክስዮን ድርሻ ገበያ ጥቃቱ ከመፈጸሙ አምስት ቀናት አስቀድሞ “በድንገት እና በከፍተኛ መጠን መጨመሩን” የአሜሪካ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ መረጃን ዋቢ አደርጎ ጠቅሷል።
“ጥቃቱ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በቴል አቪቭ የአክስዮን ገበያ የእስራኤል የአክስዮን ድርሻ ፈጣን ሽያጭ በአስገራሚ ሁኔታ ጨምሮ ነበር” ሲል ባለ 66 ገጹ ሪፖርት ጠቁሟል።
ይህንን ሪፖርት ተከትሎ የእስራኤል የአክስዮን ድርሻ ገበያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በሰጠው መግለጫ ጉዳዩ እንደሚታወቅ ገልጾ የሚመለከታቸው አካላት ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁሟል።
ጥናቱ ከፈረንጆቹ መስከረም 14 ጀምሮ ጥቃቱ ሊፈጸም ሁለት ቀን እስኪቀረው ድረስ የእስራኤል ትልቁ ባንክ 4.43 ሚሊዮን አዳዲስ ድርሻዎቹን ‘በፈጣኑ መሸጣቸውን’ አመልክቷል።
“የጥናታችን ግኝት የአክስዮን ድርሻ ነጋዴዎች ቀጥሎ ስለሚመጣው ጥቃት ቀድመው ተረድተው ከዚህ አሰቃቂ ሁነት አትርፈዋል” ካሉ፣ በዚህ አይነት ሁኔታ የአሜሪካ እና ኣለም አቀፍ ድርጅቶች ያላቸው የመረጃ ልውውጥ መቀነሱን ያሳያል ብለዋል።
መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ላለፉት ሁለት ወራት ጋዛ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን፥ ይህም በእስራኤል እና በአካባቢው አገራት ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ እንዳለው ይታመናል።












