እስራኤል የሐማስን ዋሻዎች ከባሕር በሚሳብ ውሃ በማጥለቅለቅ ልታወድም ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተጀመረው ጦርነት እነሆ ዛሬ ኀዳር 26/2016 ዓ.ም. ሁለተኛ ወሩን የደፈነ ሲሆን፣ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር አስታውቃለች።
በዚህም ጋዛ በሐማስ ሰበብ ባለፉት ሁለት ወራት ከምድር፣ ከአየር እና ከባሕር በዘነበባት የቦምብ እና የሚሳኤል ውርጅኝ ሰፊ ክፍሏ የፍርስራሽ ክምር ሆኗል። አሁን ደግሞ ሐማስ ይገኝባቸዋል የተባሉትን ዋሻዎች በውሃ ልታጠፋቸው ተነስታለች።
እስራኤል የሐማስ ቡድን በጋዛ ሰርጥ “እንደ የሸረሪት ድር” ዝርግቷቸዋል የተባሉትን ዋሻዎች ከባሕር በሚሳብ ውሃ ነው ለማጥለቅለቅ ዕቅድ እንዳላት እየተነገረ ያለው።
ዎል ስትሪት ጆርናል የአሜሪካ ባለሥልጣናት ምንጮቹን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ እስራኤል፤ ሐማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋዛ ወሰጠ የዘረጓቸውን ዋሻዎች በጎርፍ አጥለቅልቃ ከጥቅም ውጪ ለማድረገ አማራጮችን እያጤነች ነው።
እስራኤል የሐማስ የደም ሥር ናቸው የምትላቸውን ከጋዛ መሬት በታች የተገነቡትን ዋሻዎች ለዓመታት ለማውደም በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ እርምጃዎችን ስትወስድ እና የተወሰኑትን ሰታወስም ቆይታለች።
ከመስከረም 26ቱ የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ ዋሻዎቹን ብቻ ሳይሆን እራሱን ሐማስን ከጋዛ ጠራርጋ ለመጠፋት የወሰነችው እስራኤል በግዛቲቱ ወስጥ ከመሬት በላይ እና በታች ያሉ የሐማስ መጠቀሚያዎችን እያወደመች ነው።
ባለፉት ሁለት ወራት እስራኤል በምድር፣ በባሕር እና በአየር ጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ የሐማስ መሸሸጊያ ናቸው ያለቻቸውን ሆስፒታሎችን ሳይቀር አጥቅታለች።
አሁን ደግሞ ለዓመታት በጥንቃቄ ከጋዛ መሬት ሥር የተገነቡትን የወታደራዊ ማዘዣዎች፣ የስንቅ እና ትጥቅ መዘጋጃ እና ማከማቻዎች፣ የተዋጊዎች መሸሸጊያ እንዲሁም መተላላፊያ ናቸው ያለቻቸውን ዋሻዎች በውሃ በማጥለቅለቅ ተነስታለች።
እስራኤል ይህን ውጥኗን ሊፈጽሙ የሚችሉ አምስት ግዙፍ ውሃ ስበው በከፍተኛ ኃይል የሚገፉ (ፓምፖች) አል-ሻቲ ከተባ መጠለያ ጣቢያ በቅርብ ርቀት ላይ መትከሏ ተዘግቧል።
እንደ የዎል ስትሪት ምንጭ ከሆነ እነዚህ ፓምፖች በሰዓት በሺዎች የሚለካ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ከሜደትራኒያን ባሕር በመሳብ በጥቂት ሳምንታት ከጋዛ መሬት ሥር ያሉ ዋሻዎችን በጎርፍ ማጥለቅለቅ ይችላሉ።

የቢቢሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ወኪል ዮላንድ ኒል ግን ይህ ዕቅድ እስራኤልን ውጤማ ሊያደርጋት ቢችልም መዘዙ ግን ከባድ ሊሆን ይችላል ትላለች።
መቀመጫዋን በኢየሩሳሌም ያደረገችው ዮላንድ፤ እስራኤል ዋሻዎቹን ከባሕር በምትስበወ ውሃ ብታጥለቀልቅ በዋሻዎቹ ውስጥ ተይዘው ይገኛሉ የተባሉት ታጋቾች ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ትላለች።
ሐማስ ከዚህ ቀደም ከእስራኤል አግቶ የወሰዳቸውን ሰዎች “በዋሻዎች ውስጥ እና ደኅንነታቸው በተጠበቁ ስፍራዎች” ደብቆ ማስቀመጡን ገልጾ ነበር።
በኳታር አደራዳሪነት ሁለቱ ኃይሎች ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ተስማምተው ስምምነቱ ለሰባት ቀናት ተፈጻሚ ሆኖ በቆየበት ወቅት የበርካታ እስረኞች እና ታጋቾች ልውውጥ ቢደርግም አሁም እስራኤል ሙሉ በሙሉ ታጋቾቿን አስለቀቅ አልጨረሰችም።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ ከ1200 በላይ ሰዎችን ገድሎ ከ240 ያላሱ ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በአየር፣ በምድር እና በባሕር ኃይሎቿ ጋዛ ላይ ቦምብ ስታዘንብ ቆይታ ሁለቱ ኃይሎች በደረሱት ስምምነት ሐማስ ከ100 ያላንሱ ከእስራኤል የታገቱ ሰዎችን ለቋል።
እስራኤል በጋዛ ላየ ለሳምንታት ባካሄደችው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ከመግደሏ በተጨማሪ 50 ታጋቾች በጥቃቶቹ መገደላቸውን ሐማስ አስታውቆ ነበር።
ዮላንድ ኒል ታዲያ ዕቅዱ በታጋቾች ሕይወት ላይ ከሚደቅነው ስጋት በተጨማሪ፤ ዋሻዎቹ በባሕር ውሃ ቢጥለቀለቁ በጋዛ ያለው ለመጠጥ የሚሆነው የከርሰ ምድር ውሃ ይበከላል በማለት ያለውን ስጋት ገልጻለች።
ይሁን እንጂ ይህን ዕቅድ ተግባራዊ ቢደረግ እስራኤል የምትፈልገውን ውጤት ልታሳካ እንደምትችል ዮላንድ የ2015ቱን የግብፅ ተሞክሮ ታስታውሳለች።
ግብፅ ከስምነት ዓመታት በፊት ከጋዛ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የተበራከተውን የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተጠቀመችው ተመሳሳይ ዘዴ ውጤታማ አድርጓት ነበር።
ግብፅ በአዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች በሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች የተገነቡትን በርካታ የዋሻ መረቦችን በሜዲትራኒያን ባሕር ውሃ በማጥለቅለቅ ከጥቅም ውጪ ማድረግ ችላ ነበር።
ዎል ስትሪት ጆርናል በዘገባው የእስራኤል መንግሥት የሐማስ ዋሻዎችን በጎርፍ የማጥለቅለቅ ዕቅዱን ከሳምንታት በፊት ለአሜሪካ ማሳወቁን ጨምሮ ዘግቧል።
ጋዜጣው ያናገራቸው የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን እስራኤል የሐማስ ዋሻዎች ከጥቅም ውጪ ለማድረግ መነሳቷ ምክንያቱን መረዳት ይቻላል ያሉ ሲሆን፤ ፍላጎቷን ለመፈጸም የተለያዩ አማራጮችን እያጤነች ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሐማስ ዋሻዎች
ሐማስ 41 ኪ.ሜትር በምትረዝመው እና 10 ኪ.ሜትር ስፋት ባላት ጋዛ ውስጥ የዘረጋቸው የዋሻዎች ብዛት እና ስፋትን በትክክል ማወቅ ያዳግታል።
ይሁን እንጂ እስራኤል “የጋዛ ምድር ውስጥ የባቡር መስመር” የሚል ስያሜ የሰጠቻቸው በሐማስ የተገነቡት ዋሻዎች መገኛ ስፍራዎችን የሚያሳይ ካርታ አውጥታለች።
እአአ በ2021 በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ግጭት በተቀሰቀሰ ወቅት የእስራኤል ጦር የአየር ድብደባ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ዋሻዎችን ማውደሙን ገልጾ ነበር።
ሐማስ የዘረጋቸው ዋሻዎቹ 500 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝሙ እና በእስራኤል ጥቃት የወደመበት 5 በመቶው ብቻ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር ከ500 ያላሱ የሐማስ ዋሻዎችን ማውደሙን ጦሩ ትናንት ማክሰኞ አስታውቋል።
ሐማስ ዋሻዎች መገንባት የተጀመረው እስራኤል ጦሯን እና ያሰፈረቻቸውን ዜጎች ከጋዛ ሰርጥ ማስውጣት ሳትጀምር ከእአአ 2005 በፊት ነበር።
ሐማስ የጋዛ ሰርጥን ከተቆጣጠር በኋላ ታዲያ ግንባታውን አጠናክሮ ቀጠለ። እነዚህ ዋሻዎች ሁሉም እዚያው ጋዛ ውስጥ ብቻ የሚቀሩ ሳይሆን ወደ እስራኤልም ዘልቀው የተገነቡ እንደነበሩ ጦሯ ደርሶበታል።
እአአ 2013 ላይ እስራኤል ድንበር የተሻገረ ዋሻ ማግኘቱ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነ ክስተት ነበር። የእስራኤሏ ኪቡትዝ ነዋሪዎች አንድ ያልተለመደ ድምጽ መስማታቸውን ተከትሎ ነበር የእስራኤል ጦር 1.6 ኪሜ የሚረዝም እና 18 ሜትር ጥልቀት ያለው ዋሻ ያገኘው።
ይህ ዋሻ ኮንክሪት ጣሪያ እና ግድግዳ ያለው ሲሆን፣ ከጋዛ ሰርጥ እስከ እስራኤሏ ኪቡትዝ የተዘረጋ ነበር።
እስራኤል በሚገኘው ሪችማን ዩኒቨርሲቲ የጦርነት ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳፍኒ ሪችመንድ-ባራክ የተለያዩ ዓይነት የሐማስ ዋሻዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የሐማስ ዋሻዎች ሁለት አይነት ናቸው። ለአንድ ዓላማ ለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰሩ እና ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚገነቡ ዋሻዎች።
“ድንበር የሚያቋርጡ ዋሻዎች ያለብዙ ድካም የሚገነቡ ናቸው። ምንም ዓይነት ምሽግም የላቸውም። የተቆፈሩት የእስራኤልን ግዛት ለመውረር በሚል ለአንድ ጊዜ ጥቅም ብቻ ነው" ይላሉ ዶ/ር ዳፍኒ።
“በጋዛ ያሉ ዋሻዎች ግን የተለዩ ናቸው። ምክንያቱም ሐማስ በመደበኛነት እየተጠቀመባቸው ነው። ረዘም ላለ ጊዜ በውስጣቸው ለመቆየትም የበለጠ ምቹ ናቸው።
“. . . አመራሮቹ በዚያ ይደበቃሉ። የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላትም አሏቸው። ኤሌክትሪክ እና የባቡር ሀዲድ የተዘረጋላቸውም ናቸው። ለመንቀሳቀሰም ሆነ በቀላሉ ለመቆም ያስችላሉ" ብለዋል።
ሁለት ወር በሞላው የሐማስ ጥቃት የተቆጣችው እስራኤል ቡድኑን ለመበቀል እና ከጋዛ ለመጥፋት ማንኛውንም እርምጃ እንደምትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሯ አና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናቷ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
እናም ባለፉት ሁለት ወራት ሠራዊቷ ከምድር በላይ ያሉ የሐማስ ይጠቀምባቸዋል የተባሉ ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የእምነት ቦታዎችን ሳየቀረ በኃያል ከንዷ ሰታወድመ ቆይታለች።
በቀጣይነተ ደግሞ ከምድር በታች ዋነኛ የሐመስ መንቀሳቀሻ ናቸው የተባሉት በብዙ ኪሎ ሜትሮች የሚረዝሙትን ዋሻዎች ከሜዲትራኒያን ባሕር በፓምፕ በምትስበው ኃይለኛ ውሃ በማጥለቅለቅ ልታወድመው ተነስታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












