አሜሪካ “በጽንፈኛ” እስራኤላውያን ላይ የቪዛ ማዕቀብ ጣለች

በዌስት ባንክ ሰፋሪ የሆነው ታጣቂ እስራኤላዊ።

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, በዌስት ባንክ ሰፋሪ የሆነ ታጣቂ እስራኤላዊ።

እስራኤል በኃይል በተያዘችው ዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን ላይ ሁከት የሚፈጥሩ ጽንፈኛ እስራኤላውያን ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሏን አሜሪካ አስታወቀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት በሚያደርሱ የእስራኤል ሰፋሪዎች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

እገዳው በአመጽ በተከሰሱ ፍልስጤማውያን ላይም ተግባራዊ ይሆናል ሲሉ አክለዋል።

በጋዛ ሰርጥ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በዌስት ባንክ ጥቃቶች ተበራክተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር እገዳው "በደርዘን የሚቆጠሩ" አክራሪ እስራኤላውያን እና የቤተሰባቸውን አባላት የሚመለከት ነው ብለዋል። አሜሪካ የቪዛ ክልከላ የጣለችባቸውን ሰዎች ማንነት በሕጋዊ ምክንያት ይፋ ማድረግ አትችልም።

እርምጃው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእስራኤል መንግሥት በሰፋሪዎች ላይ ያለውን አቋም በተመለከተ ዋሽንግተን ልዩነት እንዳላት ያሳያል ተብሏል። ሰፋሪ የሆኑት ከፍተኛ የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሮቹ ኢታማር ቤን-ግቪር እና ቤዛሌል ስሞትሪች በዌስት ባንክ ያለውን ሁከት ለማቃለል ይፈልጋሉ በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጋዛ ያለውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ የእስራኤል ሰፋሪዎች መሬት በኃይል ለመውረር አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ነው።

እአአ በ1967 ከተካሄደው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እስራኤል ዌስት ባንክን እና ምስራቅ እየሩሳሌምን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተቆጣጠረች በኋላ ከ700 ሺህ በላይ አይሁዳውያን ከ250 በላይ ሰፈራዎች ውስጥ ይኖራሉ። አብዛኛው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰፈራውን በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ህገወጥ ነው ቢሉም እስራኤል እና አሜሪካ ግን የአተረጓጎም መዛባት አለ ሲሉ ይከራከራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመስከረም 26 የጦርነቱ መጀመር በኋላ ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ 314 ጥቃቶች ማድረሳቸው መመዝገቡን ገልጿል። በተመሳሳይ ወቅት በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ባደረሱት ጥቃት ሦስት የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ አራት እስራኤላውያን ተገድለዋል።

"በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ላይ የኃይል ጥቃት ያደረሱ አክራሪ ሰፋሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግ ለእስራኤል መንግሥት ገልጸናል። ፕሬዝዳንት ባይደን ደጋግመው እንደተናገሩት ጥቃቶቹ ተቀባይነት የላቸውም" ብለዋል ብሊንከን በሰጡት መግለጫ።

ይህ ቪዛ ክልከላ ውሳኔ የተሰማው የእስራኤል ዜጎች ከቪዛ ነጻ ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ የሚፈቅደውን የአሜሪካ የቪዛ ፕሮግራም እስራኤል መቀላቀሏ ይፋ ከሆነ ከአንድ ወር በኋላ የመጣ ነው።

ማክሰኞ በወጣው ውሳኔ መሠረት ውሳኔው የተላለፈባቸው ግለሰቦች ለፕሮግራሙ ብቁ አይሆኑም ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ቀድሞ የአሜሪካ ቪዛ ያላቸውም የመግቢያ ፈቃዳቸው ይሰረዛል ተብሏል።

የአሜሪካ ፓስፖርት የያዙ ግለሰቦች ግን አዲሱ ፖሊሲ አይመለከታቸውም።

የአሜሪካን ውሳኔ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት "በሚያሳዝን ሁኔታ ልናወግዘው የሚገባን የአክራሪዎች ጥቃት አለ" ብለዋል።

"እስራኤል ሕግ የሚከበርባት ሀገር በመሆኗ ኃይልን የመጠቀም መብት ለተፈቀደላቸው ሰዎች ብቻ የተሰጠ ነው" ብለዋል።