የኬንያ ምርጫ፡ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን አልቀበልም አሉ

ራይላ ኦዲንጋ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ራይላ ኦዲንጋ

በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን አልቀበልም አሉ።

ትናንት ነሐሴ 9/2014 ዓ.ም. የአገሪቱ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን 5ኛውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር እና በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚደገፉት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱ ውድቅ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ራይላ ዛሬ ነሐሴ 10/2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የኮሚሽኑ ዋና ሰብሰባዊ ዋፉላ ቼቡካቲ ይፋ ያደረጉትን የምርጫውን ውጤት ውድቅ ለማስደረግ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።

ራይላ የኮሚሽኑን ዋና ሰብሰቢ ዋፉላ ቼቡካቲን "አምባገነን” ብለው በመጥራት አጥብቀው ተችተዋቸዋል።

“ትናንት ቼቡካቲ ይፋ ያደረጉትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አንቀበለውም” ብለዋል ራይላ።

ከፍተኛ ደጋፊ ያላቸው ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለታቸው በአገሪቱ ምርጫውን ተከትሎ ግጭት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከአሁኑ አይለዋል።

ራይላ የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ሲያደርጉ የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት በመተላለፍ ትልቅ የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ብለዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ጨምረው በገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች መካከል ልዩነት እያለ ዋፉላ ቼቡካቲ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ስህተት ነው ብለዋል።

የኬንያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ያስፈጸመው ገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን 7 ኮሚሽነሮች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራቱ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤቱ አለመስማማታቸውን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሮቹ በሰጡት መግለጫ “ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ለውጤቱ ኃላፊነት መውሰድ አንችልም” ብለው ነበር።

አራቱ ኮሚሽነሮች ዋፉላ ቼቡካቲ ትናንት ይፋ ያደረጉት አራቱ እጩዎች ያገኙት አጠቅላለ የድምጽ አማካይ ውጤት ድምር ከ100 ፐርሰንት በላይ ሆኗል ብለዋል።

ቼቡካቲ የዘረዘሩት የአራቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ድምር 100.01 በመቶ ሲሆን ከአጠቃላይ ከተሰጠው ድምጽ 0.01 በምርጫ ውጤት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለዋል ኮሚሽነሮቹ።

ለምርጫው ውጤት ኃላፊነት አንወስድም ያሉት አራቱ ኮሚሽነሮች
የምስሉ መግለጫ, ለምርጫው ውጤት ኃላፊነት አንወስድም ያሉት አራቱ ኮሚሽነሮች

ምርጫው የኬንያውያንን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ይበሉ እንጂ ዋፉላ ቼቡካቲ ትናንት የምርጫ ውጤቱን ይፋ ሲያደርጉ ውጤቱ የኬንያውያን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

"ማስፈራራት እና ትንኮሳዎች ቢደርሱብኝም እናንተ ፊት ለመቆም ችያለሁ። ኃላፊነቴን በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሰረት ተወጥቻለሁ” ሲሉ ቼቡካቲ ተናግረዋል።

ቼቢካቲ ፕሬዝዳንታዊ ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ በምርጫው ሂደት ላይ “ማስፈራራቶች፣ ዛቻዎች እና ትንኮሳዎች ቢደርሱብኝም እናንተ ፊት ለመቆም ችያለሁ። ኃላፊነቴን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሰረት ተወጥቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ምርጫውን እንዳሸነፉ የታወጀላቸው ዊሊያም ሩቶ የምርጫ ኮሚሽኑ ባልደረቦች ተዓማኒ በሆነ መልኩ ምርጫውን ማስፈጸም በመቻላቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።