42 ሴቶችን ገድሏል በተባለው ኬንያዊ ዙሪያ ምላሽ ያላገኙ አወዛጋቢ ጉዳዮች

ኬንያውያንን ያስደነገጠው የ42 ሴቶች አሰቃቂ ግድያ ፈጻሚ ነው የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ሰኞ ዕለት አስታውቆ ነበር።

አሰቃቂው የወንጀል ድርጊት ሕዝቡን ከማስደንገጡ በተጨማሪ ግለሰቡ እንዴት በቁጥጥር ስር ዋለ? የሚለውም ለበርካቶች እንቆቅልሽ ሆኗል።

የ33 ዓመቱ ኮሊንስ ጁማይሲ ካሉሻ ሚስቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን መግደሉን እንዳመነ ፖሊስ ገልጿል።

ሆኖም የግለሰቡ ጠበቃ ተጠርጣሪው ግድያዎቹን ፈጽሜያለሁ ብሎ እንዲናዘዝ በፖሊስ ስቃይ ተፈጽሞበታል ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

ግለሰቡ ገድሏቸዋል ከተባሉት ሴቶች መካከል የዘጠኙ አካላት ተቆራርጦ እና በማዳበሪያ ውስጥ ተቋጥሮ የተገኘው ባከፈው ሳምንት ነው።

የሴቶቹ አስከሬን በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ መገኘቱም ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ሆኗል።

አስከሬኖቹ ከፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ እንዴት ሊገኙ ቻሉ?

በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ሴቶች የተቆራረጠ አካላት የተገኙት በናይሮቢ የጨረቃ ሰፈር ተብለው ከሚጠሩት አንዱ በሆነው ሙኩሩ ክዋ ንጄንጋ በተባለ ስፍራ ነው።

በርካቶችን ግራ ያጋባው አስከሬኖቹ የተገኙት ከአንድ ፓሊስ ጣቢያ 100 ሜትር ርቀት ላይ መሆኑ ነው። በዚህም ፖሊስ እንዴት ነው አስከሬኖቹን ማየት ያልቻለው የሚለውም ጉዳይ ጥያቄ ፈጥሯል።

ከወንጀሉ ጋር ተያይዞም ነዋሪዎች ባለሥልጣናቱን “ቸልተኝነት እና ሙያዊ ብቃት የጎደላቸው ናቸው” ሲሉ ተችተዋቸዋል።

በምላሹም የኬንያ ፖሊስ ጊዜያዊ ኃላፊ ዳግላስ ካንጃ በስፍራው የሚገኘው ክዋሬ የተሰኘው ፖሊስ ጣቢያ መኮንኖች ወደ ሌላ ፖሊስ ጣቢያ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን እሁድ ዕለት አስታውቀዋል።

ፖሊሶቹ ከመዛወራቸው በፊት በአቅራቢያቸው የተገኙ አስከሬኖችን እንዴት መለየት ተሳናቸው? በሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደሆነ ግልጽ አልተደረገም።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳው የኬንያ ፖሊስ ከእነዚህ ሟቾች ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን በሚለው ላይ ምርመራ መክፈቱንም የፖሊስ ተቆጣጣሪ አስታውቋል።

ይበልጥ ሁኔታውን ደግሞ ግራ የሚያጋባው አስከሬኖቹ የተገኙበት መንገድ ነው።

ደብዛዋ ጠፍቷል የተባለችው የጆሴፊን ኦዊኖ አንዲት የቤተሰብ አባል እንደምትለው የተፋችው ጆሴፊን ለአንዳቸው “በህልማቸው” ታይታ ያለችበትን ትክክለኛ ስፍራ በመጠቆም እንደረዳቻቸው ገልጻለች።

የጆሴፊን የአጎት ልጅ ዲያና ኬያ ለሲቲዝን ቲቪ እንደተናገረችው ያለችበትን ስፍራ በህልም ከተገለጸችላቸው በኋላ ቤተሰቡ በቆሻሻ ክምሩ ውስጥ እንዲፈልጓት ለወጣቶች ከፍለው ማፈላለግ ጀመሩ።

በዚህም መንገድ ነበር ዘጠኝ አካላቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተቆራረጡ ሴቶች አስከሬኖች ባለፈው ሳምንት አርብ የተገኙት።

አካላቸው የተቆራረጡት አስከሬኖች በፕላስቲክ ከረጢት ተሸፍነው በገመድ ታስረው ነበር።

ከማኅበረሰቡ በተገኘ ጥቆማም ፖሊስ ሁኔታውን መረዳቱን ነው በመጀመሪያው መግለጫው ላይ ይፋ ያደረገው።

በኋላም የወንጀል መርመራ ዳይሬክቶሬት መሐመድ አሚን ስለ ሁኔታው ተጠይቀው ሲመልሱ “ህልም አላሚዎች አይደለንም እንዲሁም በህልም አናምንም” ብለዋል።

አስከሬኖቹ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው በስፍራው የተጣሉት?

የተገኙት አስከሬኖች በተለያየ የመበስበስ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ፖሊስ፤ ይህም ሴቶቹ በተለያየ ጊዜያት ውስጥ መገደላቸውን ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት አወዛጋቢ በሆነው ሴቶቹን ገድያለሁ በሚል የተናዘዘው ግለሰብ መጀመሪያ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መግደሉን ማመኑን ፖሊስ ገልጾ ነበር። ሆኖም አስከሬኖቹ የተጣሉት በዚያን ወቅት ነው ወይስ በቅርብ ጊዜ ነው የሚለው ግልጽ አይደለም።

ሃኪ አፍሪካ የተሰኘው የመብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሑሴን ካሊድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፖሊስ መግለጫ “በርካታ ክፍተቶች” እንዳሉበት ነው።

ፖሊስ ግለሰቡን እንዴት በፍጥነት በቁጥር ስር ሊያውል ቻለ?

ፖሊስ ግድያው ተፈጽሟል ከተባለበት ለሁለት ዓመታት ያህል ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሳይኖረው አስከሬኑ በተገኘበት ከሦስት ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዴት ‘ገዳዩን’ በቁጥጥር ስር ሊያውል ቻለ? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል።

ግለሰቡ ባለፈው እሁድ የአውሮፓ ፍጻሜ እግር ኳስ ጨዋታን በአነስተኛ መጠጥ ቤት እየተመለከተ እያለ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውየዋለሁ ብሏል።

አስከሬኖቹ ከተገኙበት ስፍራ አቅራቢያ ከሚገኘው የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ተገኝተዋል የተባሉትን አንዳንድ እቃዎች ፖሊሶች ለመገናኛ ብዙኃን አሳይተዋል። እነዚህም 10 ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ላፕቶፕ፣ መታወቂያ ካርዶች እንዲሁም የሴት ልብስ ይገኙበታል።

ፖሊስ ካሉሻ ያለበትን ስፍራ ለማወቅ የቻለው ሰለባ ከሆኑት ውስጥ የአንዷ ስልክ የሚገኝበት ቦታ ላይ ክትትል በማድረግ እንደሆነም አሳውቋል። የካሉሻ ጠበቃ በበኩሉ የማስረጃውን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ ከትተውታል።

የዚህ አሰቃቂ ግድያ ሰለባዎች እነማን ናቸው?

እስካሁን መለየት የተቻለው አንደኛዋን ነው - የ25 ዓመቷን ሮዝሊን ኦንጎጎ።

ወንድሟ ኢማኑኤል ኦንጎጎ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሮዝሊን ሰኔ 21/2016 ዓ.ም ሥራ ፍለጋ ከቤት ከወጣች በኋላ ደብዛዋ ጠፋ። ከቆሻሻ ስፍራው የወጡ አስከሬኖች ወደ አስከሬን ማቆያ ስፍራ መወሰዳቸውን ተከትሎም የሮዝሊን ቤተሰቦች ወደዚያው አቀኑ።

በጠፋችበት ዕለት በለበሰችው ልብስ እና በፀጉር አሰራሯ ሮዝሊንን መለየት እንደቻሉም ቤተሰቧ አባላት አስረድቷል።

ፖሊስ በበኩሉ ካሉሻ የገደላት የመጀመሪያው ሰለባ ባለቤቱ እንደነበረች እና መታወቂያዋም ከሌሎች ሰለባዎች ንብረቶች መካከል ተገኝቷል ብሏል።

የጠፋችውን አባላቸውን በህልም ያለችበትን ስፍራ አውቀናል ያሉት የጆሴፊን ቤተሰቦችም አስከሬኗን ለመለየት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖሊስ በኬንያ ስላለው የሴቶች ደኅንነት ምን ይላል?

በአሁኑ ወቅት የእነዚህ አስከሬኖች በቆሻሻ ስፍራ መገኘት ከጥቂት ወራት በፊት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ የተገኘችውን የ20 ዓመቷን ሪታ ዋይኒን ጉዳይ ቀስቅሷል።

ተገድላ የተቆራረጠው አካሏ የተገኘው ናይሮቢ ውስጥ ለአጭር ጊዜ በሚከራይ አፓርንትንመት ክፍል ውስጥ ነበር። የሪታ ዋይኒ ጉዳይ ገና እልባት አላገኘም።

የሪታ ግድያ በሴቶች ላይ ባነጣጠረው ግድያ (ፌሚሳይድ) እንዲሁም ሌሎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመቃወም ለሚደረጉ አገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፎች መነሻ ሆኗል።

በኬንያ ከ2016 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ500 በላይ ሴቶች ሆን ተብሎ ሴቶች ላይ ባነጣጠረው ግድያ ለሕልፈት መዳረጋቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ገልጿል።

አሁንም በናይሮቢ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ አካላቸው ተቆራርጦ የተገኙትም በሙሉ ሴቶች ናቸው።

የተወሰኑ የአገሪቱ መንግሥት ሴት ባለሥልጣናት የአስከሬን ማቆያ ስፍራውን ከጎበኙ በኋላ ምርመራው እንዲፋጠን እና እንዲህ ዓይነት መሰል ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ፖሊስ በሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ምን እያደረገ እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቃለ አቀባይ ሬስላ ኦንያንጎ ለዚህ በተለየ መልኩ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ነገር ግን የፖሊስ ሥራ “የሁሉንም ሰዎች ሕይወት እና ንብረት መጠበቅ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።