ከአሜሪካ የተባረሩ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ስደተኞች ሩዋንዳ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, PA
ሩዋንዳ 250 ስደተኞችን ለመቀበል ከፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳዳር ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት የመጀመሪያዎቹ ሰባት ስደተኞች ኪጋሊ ደረሱ።
የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዮላንድ ማኮሎ ሰባት ስደተኞችን የያዘው የመጀመሪያው ቡድን ነሐሴ አጋማሽ ላይ ሩዋንዳ መግባቱን አረጋግጠዋል።
ቃል አቀባይዋ፣ ሩዋንዳ ከገቡት ስደተኞች መካከል አራቱ በአገሪቷ እንደሚቆዩ እና ሦስቱ ደግሞ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ከመግለጽ በዘለለ ስለስደተኞቹ ዜግነት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ስደተኞች ስቅይት እና ጥቃት ሊደርስባቸው ወደሚችልባቸው አገር የሚላኩ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ስደተኞችን የማባረር እርምጃ ዓለም አቀፍ ሕግን ሊጥስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ጥር ወር ላይ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ አንስቶ በአሜሪካ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ስደተኞችን በጅምላ የማባረር ፕሮግራም ላይ ትኩረት አድርገዋል። እስካሁንም በርካታ አገራት ከሌሎች አገራት የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል።
የአገሪቷ ቃል አቀባይ ማኮላ የሩዋንዳ መንግሥት ደጋፊ ለሆነው ኒው ታይምስ ኒውስ ሳይት እንደተናገሩት "እነዚህ ስደተኞች በሩዋንዳ መንግሥት ተገቢው ድጋፍ እና ጥበቃ ይደረግላቸዋል" ብለዋል።
ስደተኞቹ በዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የሚቆዩ ሲሆን በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና በሩዋንዳ ማኅበራዊ አገልግሎት እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።
የአይኦኤም ቃል አቀባይም የስደተኞቹ መሠረታዊ ፍላጎት መሟላቱን ለመገምገም ስደተኞቹን መጎብኘቱን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል የገለጹ ሲሆን ስለሁኔታው ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ማኮሎ ለቢቢሲ ሲናገሩ ሩዋንዳ ስምምነቱን የተቀበለችው " እያንዳንዱ ሩዋንዳውያን በሚባል ደረጃ የመፈናቀልን ውጣ ውረድ ስለተመለከቱ ችግሩን ስለሚረዱ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ሩዋንዳ እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የዘር ጭፍጨፋ ውስጥ ያለፈች ሲሆን የአገሪቷ መንግሥት የሌሎች አገር ስደተኞችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
ምንም እንኳን አገሪቷ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ትችት ቢገጥማትም ለስደተኞቹ ምቹ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ እንዲሆን እየሰራሁ ነው ብላለች።
ከስድስት ዓመት በፊት ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት በሊቢያ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው የነበሩ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ተያቂዎች በመስከረም 2019 እና በሚያዝያ 2025 መካከል ውስጥ ባሉት ጊዜያት ወደ ሩዋንዳ ተልከዋል።
ሩዋንዳ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋርም መሠል ስምምነት የነበራት ሲሆን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሩዋንዳ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በ2022 ከወግ አጥባቂው መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሳ ነበር።
ሆኖም ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የሰራተኛ ፓርቲው መሪ ሰር ኬር ስታርመር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዩኬ በርካታ የሕግ ጥያቄዎች ሲነሱበት የነበረውን ይህንን ስምምነት ሽራለች።
ዩኬ በስምምነቱ መሠረት ለሩዋንዳ 310 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ የከፈለች ሲሆን ለጥገኝነት ጠያቂዎች ቤት እየገነባች ነበር። አሁን ላይ እነዚህ ቤቶች ምን እንደሆኑ ግልጽ መረጃ የለም። ሩዋንዳ በቅርቡ ከአሜሪካ ጋር ለደረሰችው ስምምነት የገንዘብ ክፍያ መኖር አለመኖሩም ግልጽ አይደለም።
ሰኔ ወር ላይ የትራምፕ አስተዳደር በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ መካከል ለሦስት አስርተ ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ያለመ የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ማፈራረሙ ይታወሳል።
ኪጋሊ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰውን ኤም 23 አማጺ ቡድን ትደግፋለች በሚል የምትከሰስ ሲሆን እርሷ ግን ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።















