ሩዋንዳ ከአሜሪካ የሚባረሩ 250 የሌላ ሀገር ስደተኞችን ለመቀበል መስማማቷን ገለጸች

የሩዋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency/Getty Images

ሩዋንዳ፤ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር የተደረገ ስምምነትን ተከትሎ እስከ 250 የሚደርሱ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ልትቀበል መሆኑን አስታወቀች።

በስምምነቱ መሰረት ከአሜሪካ የሚመጡት ስደተኞች "የስራ ክህሎት ስልጠና፣ የጤና እንክብካቤ እና በሩዋንዳ ህይወታቸውን ለመጀመር የሚያስችላቸው ማረፊያ" እንደሚሰጣቸው የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሩዋንዳ እዚህ ስምምነት ላይ ስትደርስ፤ በሀገሪቱ "እንዲሰፍሩ የሚቀርቡትን እያንዳንዱን ግለሰብ የማጽደቅ አቅም" በቅድመ ሁኔታነት መቀመጡንም ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

ዋይት ሀውስ ይህንን ስምምነት በተመለከተ በቀጥታ አስተያየት አልሰጠም። ነገር ግን "[የቀድሞው ፕሬዝዳንት] ጆ ባይደን" ወደ አሜሪካ "ሰርገው እንዲገቡ" የፈቀዱላቸውን "ህገወጥ የውጭ ዜጎችን ለማስወገድ" ከሚረዱን ሀገራት ጋር በተከታታይ ንግግር እያደረግን ነው ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

ትራምፕ፤ ጥር ላይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ ሰነድ አልባ ስደተኞችን በፍጥነት ከአሜሪካ ለማስወጣት ሰፊ በጅምላ የማባረር መርሃ ግብር ላይ ትኩረት አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል ከገቧቸው ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይህ ነበር።

ሩዋንዳ እና አሜሪካ የዚህ አይነቱ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣት የጀመሩት ግንቦት ላይ ነበር።

ይህ የሆነውም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ " እጅጉን ከተናቁ የሰው ልጆች የተወሰኑት" ሲሉ የገለጿቸውን ስደተኞች መቀበል የሚችሉ ሀገራት "በብርቱ እየተፈለጉ" መሆኑን መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር፤ ሊያባርር የሚፈልጋቸው ነገር ግን ሀገራቸው የማትቀበላቸውን ስደተኞችን እንዲረከቡት ለማድረግ ሲል ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል። ስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን ፍርደኛ ወንጀለኞችን ጨምሮ የተወሰኑ ስደተኞችን በቅርቡ ተቀብለዋል።

ቃል አቀባይዋ ማኮሎ፤ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ደረሰችው "እያንዳንዱ የሩዋንዳ ቤተሰብ በሚባል ደረጃ የመፈናቀልን ችግር ስለሚያውቀው" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሩዋንዳ ማህበረሰብ እሴቶች የተመሰረቱት "በመቀላቀል እና መልሶ ማቋቋም" ላይ መሆኑንም አክለዋል።

ስደተኞችን ለመቀበል የተገነባ የመኖሪያ ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩዋንዳ ከዚህ ቀደም ከዩናይትድ ኪንግደም ስደተኞችን ለመቀበል ከተመማማች በኋላ የተገነቡት መኖሪያዎች ያሉበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሀገራቸው "በዓለም ዙሪያ ችግር ላጋጠማቸው ስደተኞች ሌላ እድል" ለመስጠት በሚል "መንፈስ" እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ግንቦት ላይ በተናገሩበት ወቅትም ይህ አይነቱ አስተያየት ተንጸባርቆ ነበር።

ሩዋንዳ ከስድስት ዓመት ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር ስምምነት ፈጽማ የነበሩ ሲሆን ይህንን ተከትሎም ከመስከረም 2019 እስከ ሚያዝያ 2025 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሊቢያ ውስጥ መውጫ ያጡ ሶስት ሺህ ገደማ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች ወደ ሀገሪቱ ገብተዋል።

ወደ ሩዋንዳ ከተወሰዱት ስደተኞች ውጥ ብዙዎቹ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ መደረጉን የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።

ሩዋንዳ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመቀበልን በ2022 በወቅቱ ከነበረው ወግ አጥባቂ መንግስት ጋር ስምምነት አድርጋ ነበር።

ነገር ግን በርካታ ህጋዊ ተግዳሮቶች ያጋጠሙትን ይህ መርሃ ግብር፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ሌፐር ፓርቲ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ስልጣን ከያዘ በኋላ ተቋርጧል።

ዩናይትድ ኪንግደም ይህንን መርሃ ግብር ለማስፈጸም ለሩዋንዳ 240 ሚሊዮን ፓውንድ የከፈለች ሲሆን ለስደተኞች መጠለያ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ገንብታ ነበር። እነዚህ መገልገያዎች በአሁኑ ሰዓት ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ግልፅ አይደለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የሩዋንዳ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሩዋንዳ ከአሜሪካ ጋር በገባችው በዚህ ስምምነት መጠኑ ያልተገለጸ የገንዘብ ድጋፍ ታገኛለች። ነገር ግን ይህ መረጃ አልተረጋገጠም።

ቃል አቀባይዋ ማኮሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተጨማሪ ዝርዝሮች ይፋ የሚሆኑት ስምምነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን ስደተኞችን ከመጡበት ወጪ ወደ ሆነ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ማዘዋወር የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።