ትራምፕ፤ በማዕድን በበለፀገችው ኮንጎ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዴት አድርገው ለአሜሪካ ጥቅም ያውሉታል?

የአሜሪካ ባንዲራ ያለበት የኮንጎ ማዕድን አውጪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትራምፕ አስተዳደር፤ በምሥራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየውን እና ጎረቤት ሀገር ሩዋንዳ ጭምር የተሳተፈችትን ግጭት ለማቆም ያለመውን አወዛጋቢውን የሰላም ስምምነት ሂደት በመምራት ላይ ይገኛል።

በአፍሪካ እምብርት የምትገኘው የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ አሜሪካ፣ በአብዛኛው በቻይና የተያዘውን የቴክኖሎጂ እና የሰው ሠራሽ አስተውህሎት (ኤአይ) አብዮት ለማቀጣጠል የሚያስፈልጓትን የማዕድን ሀብቶች የተጎናጸፈች አገር ነች።

በዚህም የተነሳ የአሜሪካ የአሸማጋይነት ጥረቷ እምብዛም የሚያስደንቅ ተግባር አይደለም።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ እና የሩዋንዳውን መሪ ፖል ካጋሜን በመጪዎቹ ሳምንታት ያስተናግዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መሪዎቹ በአሜሪካ ቆይታቸው የሰላም ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።

ይህንን ክስተት ተጠቅመው በቀጠናው ውስጥ የአሜሪካን ኢንቨስትመንት የሚያሳድጉ ስምምነቶችን ለመፈጸም ተስፋ ያደረጉት ትራምፕ፤ "ታላቅ ድል" ሲሉ ጠርተውታል።

በአሜሪካ የሚገኘው 'ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን' ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል፤ የትራምፕ አስተዳደር "የሕዝበኝነትን ትርኢትን ከንግድ ስምምነት ጋር በማጣመር አዲስ የሰላም ስምምነት ሞዴልን" እያስተዋወቀ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ደ ዋል፤ "ትራምፕ ዩክሬን ውስጥም ይህንኑ አድርገዋል። ይህንን በማድረግ የሚገኘውን ክብር የፖለቲካ አቋማቸውን ለማሳደግ እና የአሜሪካ ጥቅም የሆኑ ማዕድናት ለማረጋገጥ ይፈልጉታል" ብለዋል።

"ቻይና ቀድሞውኑ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ያሉትን ብዙ ማዕድኖች ስለያዘች አሜሪካ እዚህ ጋር ለመድረስ እየተጫወተች ነው" ሲሉ አክለዋል።

እስካሁን ድረስ የአሜሪካ ኩባንያዎች በሁለት ምክንያቶች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢንቨስት ማድረግን በሩቁ ሲመለከቱት ቆይተዋል። የመጀመሪያም ምክንያት ከደህንነት ስጋት የሚመነጭ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ "የደም ማዕድናት" በመባል የሚታወቁት እነዚህ ሀብቶች፤ አማጺያንን በገንዘብ ለመደገፍ ከመዋላቸው ጋር የሚያያዝ "የስነ ምግባር ስጋት" ነው።

አሁን ግን የትራምፕ አስተዳደር የሰላም ሞዴሉን ተግባራዊ ሲያደርግ ይህ አቋም ሊለወጥ ይችላል።

ፕሮፌሰር ደ ዋል እንደሚያስረዱት ይህ ሁኔታ እንደ ሱዳን ባሉ ሌሎች ግጭት በተከሰተባቸው አገራትም ሊከሰት ይችላል።

ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው የሰላም ጥረቶች የከሸፉበት የትራምፕ አስተዳደር፤ እንደ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ግብጽ ካሉ የአረብ አገራት ጋር በመሆን በአዲስ የአሸማጋይነት ጥረቶች ውስጥ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር የሰላም ሞዴል እንዲሁ በደፈናው ሊጣል እንደማይችል ይገልጻሉ።

በተለይም ይህ ሞዴል፤ በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀውን እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እንዲሁም ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ውጊያ የሚያስቆም ከሆነ አስፈላጊነቱ እንደሚጎላ ይጠቁማሉ።

የባቡር ሃዲድ አጠገብ የተቀመጡ እስያውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና የአንጎላን የባቡር መስመር በማሻሻል በምላሹ የአገሪቱን ነዳጅ አግኝታለች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሮፌሰር ደ ዋል፤ "ትራምፕ የተለያዩ ወገኖች እንዲነጋገሩ ለማድረግ እና ነገሮችን መነቅነቅ ይችላሉ" በማለት ይናገራሉ።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ሕግ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሃንሪ ሞስተርት ግን ዴሞክራቲክ ኮንጐ "በማዕድናቶቿ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ልትጥል ትችላች" በማለት ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኮንጎ ግልጽ ያልሆነ ለደህንነት ዋስትናዎች ለማግኘት ስትል ራሷን ለዓመታት በሚቆይ ስምምነት ልታስር ትችላች ይላሉ።

ፕሮፌሰር ሞስተርት፤ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ቻይና እና ሩሲያ በበርካታ የአፍሪካ ግዛቶች ውስጥ ከተከተሏቸው "የሀብት ልውውጥ" ስምምነቶች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያስታውሳሉ።

ቻይና በአንጎላ ለገነባችው መሠረተ ልማት፤ ነዳጅ መውሰዷን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር ሞስተርት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ "የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እንኳ አንጎላ የበለጠ ዋጋ ማግኘት አልቻለችም" ሲሉ የሚያስከትለውን መዘዝ አንስተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2023 ባወጣው መረጃ ኮንጎ 25 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የማዕድን ክምችት እንዳላት ገልጿል።

ከእነዚህ የማዕድን ሀብቶች መካከል በኮምፒውተሮች፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ በሞባይል ስልኮች፣ በነፋስ ተርባይኖች እና በወታደራዊ ሀርድዌር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ የኤሌክትሮኒክስ ክፍሎችን ለማምረት የሚያስፈልጉት ኮባልት፣ መዳብ፣ ሊቲየም፣ ማግኒዝየም እና ታንታለም ይገኙበታል።

ፕሮፌሰሯ፤ "ኮንጎ የኮባልት ሀብቷን ለአሜሪካ ባለሀብቶች መስጠት ያለባት ለምን ያህል ጊዜ ነው? ለ20 ዓመት ወይስ ለ50 ዓመት? የሰላም ዋጋ ምንድነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ በመጋቢት ወር ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም እንዳረጋገጡት፤ ሀገራቸው ለምታገኘው የደህንነት ስምምነት "አንዳንድ ወሳኝ ማዕድናት" ለአሜሪካ ማቅረብ ትፈልጋለች።

አማጺው የኤም23 ቡድን፤ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘር በምስራቃዊ የኮንጎ የሚገኙ ሰፊ አካባቢዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ ድንበሩን በማቋረጥ ማዕድናትን ወደ ሩዋንዳ ማዕድናትን እየላከ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ባወጡት ሪፖርት ገልጸዋል።

ማዕድናቱ ወደ ሩዋንዳ ከገቡ በኋላ ከአገሪቱ ምርቶች ጋር እንደሚቀላቀሉ የሚናገሩት የተመድ ባለሙያዎች፤ "ከዚያ በኋላ ወደ ታች ላሉት ሌሎች የድርጊቱ ተሳታፊዎች የሚላኩበት መጠን ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

በኮንጎ የማዕድን ቁፋሮ ጉድጓዶችን ከላይ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Monusco

የምስሉ መግለጫ, በኮንጎ የማዕድን ቁፋሮ ጉድጓዶች

የመንግሥታቱ ድርጅት ኮንጎ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሩዋንዳ ወታደሮች እንዳሉት ማስረጃ ቢያቀርብም፤ ኪጋሊ፣ ኤም 23ን ትደግፋለች በሚል የሚቀርብባትን ክስ ታስተባብላለች።

አሜሪካ የሕገወጥ ማዕድን ዝውውር ጉዳይን ለመፍታት በሚመስል ሁኔታ ኮንጎ እና ሩዋንዳን የሚያስተሳስር "ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ማዕቀፍ" አቅርባለች። ሁለቱን ተፎካካሪ አገራት ለማስተሳሰር የቀረበው ሀሳብ ገና ድርድር የሚካሄድበት ነው።

ይህ ማዕቀፍ "ሕገወጥ የኢኮኖሚ መስመሮች እንዲታገዱ" እና "በተለይም ለቀጠናው ሕዝብ ለበለጠ ብልጽግና" የሚያመጡ እንዲሁም "ሁለቱንም የሚጠቅሙ የአጋርነት እና የኢንቨስትመንት ዕድሎች" እንዲፈጠሩ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ትራምፕ፤ የሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች በሰኔ 20/2017 ዓ.ም. በዋሽንግተን የሰላም ስምምነት ከመፈራረማቸው አስቀድመው ባደረጉት ንግግር "በዚህ [ስምምነት] ከኮንጎ በርካታ የማዕድን መብቶችን እናገኛለን" ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው 'ኢንስቲትዩት ፎር ሴክዩሪቲ ስተዲስ' የተባለ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ኮንጎሊዙ ብራም ቬረልስት፤ የአሜሪካ እንቅስቃሴ የዋሽንግተን የቅርብ አጋር በሆነችው በኳታር ከሚመራ ሌላ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እየሄደ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቬረልስት እንደሚናገሩት አሜሪካ እና ኳታር እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ነው። የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት ቀጣናዊ ጉዳዮችን እንደሚመለከት ጠቅሰዋል።

የኳታር ትኩረት ደግሞ በኮንጎ መንግሥት እና ኤም23 አማፂ ቡድን መካከል ባሉ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ነው። አማጺው ቡድን በምሥራቃዊ የአገሪቱን ክፍል የሚገኘውን ጎማ የተባለ የክልል ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ የራሱን አስተዳደር አቋቁሟል።

ቀጣናውን ጉዳይ የሚከታተሉት የካናዳ ፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጄሰን ስተርንስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኳታር ልክ እንደሌሎች በነዳጅ የበለጸጉ የባህረ ሰላጤው አገራት ሁሉ "ኃይልን፣ ተጽዕኖን ለማሳየት፣ ግን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችንም ለመፈለግ" ስትል በአፍሪካ ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ እያሰፋች ነው።

ኳታር በድርድር ጥረቶች ውስጥ መሳተፍ የጀመረችው፤ አሜሪካ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትወግናለች የሚል ቅሬታ ያላት ሩዋንዳ ባቀረበችው ጥያቄ አማካኝነት እንደሆነ አክለዋል። ዋሽንግተን ግን ይህንን ወቀሳ አስተባብላለች።

ፕሮፌሰር ስተርንስ እንደገለጹት ኳታር ሩዋንዳ ውስጥ "ትልቅ" ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች አሏት።

የባህረ ሰላጤዋ አጋር በኪጋሊ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የወጣበት አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች መሆኑን እና በሀገሪቱ ብሄራዊ አየር መንገድ ውስጥ የ49 በመቶ ድርሻ ለማግኘት ንግግር ላይ መሆኗን አስታውሰዋል።

ሰኔ 20 በተፈጸመው የሰላም ስምምነት መሠረት የኮንጎ እና ሩዋንዳ በ30 ቀናት ውስጥ "የደህንነት ማስተባበሪያ ስርዓት" ለማስጀመር ተስማምተዋል።

መኪና ላይ የተጫኑ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የተኩስ አቁሙ ማክሰኞ ዕለት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ቬረልስት፤ በመቀጠልም የኮንጎ መንግሥት እና ኤም23 ቀድሞውኑ በተደራደሩበት "የመሠረታዊ መርሆዎች መግለጫ" ላይ በመመስረት እስከ ነሐሴ 12 ድረስ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ይፈርማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በኮንጎ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ተንታኝ ኦኔስፎር ሴማቱምባ እንደሚናገሩት፤ ትራምፕ ጥር ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ስልጣንን ከተረከቡ ወዲህ አሜሪካ እና ኳታር "በሪከርድ በሆነ ጊዜ" ውስጥ ስምምነቶችን እያስፈጸሙ ነው።

ሴማቱምባ፤ የሁለቱ ጣልቃ ገብነት የመጣው ከ2022 ጀምሮ ሲካሄዱ የነበሩ እና በአፍሪካ አገራት የተመሩ የተለያዩ የድርድር ጥረቶች ጀምሮ " ተፋላሚዎቹ አንድም እንኳ ሰነድ እንዲፈርሙ ማድረግ ባለመቻላቸው ነው" ብለዋል።

"የቀጣናው አካላት [እንደ እነ አሜሪካ] በኪጋሊ እና በኪንሻሳ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያስችል ተመሳሳይ አቅም የላቸውም" ብለዋል።

ሴማቱምባ፤ "በስምምነቱ መፈረም እና በሰላም መስፈን መካከል ያለው መንገድ ረጅም ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ኬዝም ሂደቱ ረጅም ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አንደኛው ቁልፍ ጥያቄ፤ የኮንጎ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ኤም23 በቁጥጥሩ ስር ያሉትን ግዛቶች ያስረክባል ወይ የሚለው ነው።

ኤም23 በመላው በመላው ኮንጎ "የመንግሥት ስልጣን" እንዲቋቋም መስማማቱን የሚገልጹት ሴማቱምባ፤ ይሁን እንጂ አማፅያኑ "አንድ ሴንቲ ሜትር" መሬት እንኳ እንደማይለቁ ተናግረዋል ብለዋል።

"ሽግግሩ ቀስ በቀስ የሚካሄድ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። ለአንዳንድ አካባቢዎች ላይም የጋራ አስተዳደር ሊኖር ይገባል። ግን ሁሉም ነገር በአደራዳሪዎቹ ጥንቃቄ እና በመሃላቸው ያለውን ግድግዳ የማፍረስ ችሎታቸው ላይ የተመሰረተ ይሆናል" ሲሉ አክለዋል።