የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት እና የኤም23 አማፂያን በኳታር የሰላም ማዕቀፍ ላይ ተፈራረሙ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ኤም 23 በዶሃ የሰላም ማዕቀፍ በተፈራረሙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ኤም 23 በዶሃ የሰላም ማዕቀፍ በተፈራረሙበት ወቅት

በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም23 አማፂያን እና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ማዕቀፍ ተፈራሙ።

ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ከአሜሪካ እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን በሃብት በበለጸገው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ስትሞክር በነበረችው ኳታር ነው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኤም23 የምሥራቃዊውን ክልል ዋና ዋና ከተሞች፣ ጎማ እና ቡካፂን ተቆጣጥሯል። ቀደም ሲል ሰላምን ለማስፈን የተደረጉት ሙከራዎች አልተሳኩም።

የአሜሪካ የአፍሪካ አምባሳደር ማሳድ ቡሎስ ሰነዱ ስምንት መርሆዎችን ያካተተ መሆኑን ገልፀው፣ አብዛኛዎቹ አሁንም ሥራ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። የእስረኞች ልውውጥ እና የተኩስ አቁም ክትትል ከመጀመሪያው ከተጠበቀው በላይ የዘገየ እንደነበርም አምነዋል።

ኪንሻሳ የሩዋንዳ ወታደሮችን ከግዛቷ እንዲወጡ እየጠየቀች ነው።

ኪጋሊ ይህ በኮንጎ የሚገኘው የዲሞክራቲክ ፎርስ ፎር ዘ ሊብሬሽን ኦፍ ሩዋንዳ (ኤፍዲኤልአር) አማፂ ሚሊሻ ሲፈርስ ሊሆን እንደሚችል ተናግራለች። ቡድኑ በአብዛኛው የተዋቀረው ከ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ጋር የተያያዙት የሁትሱ ጎሳ አባላት ናቸው።

አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው ብሎስ አዲሱ ማዕቀፍ የሰብዓዊ ተደራሽነትን፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስ እና የፍትህ አካላትን ጥበቃም ይመለከታል ብለዋል።

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የጦር ኃይሎች አባል የሆነ አንድ ወታደር የተገጠመለት መትረየስ ይዞ በጃንዋ፣ ሳኬ ከተማ መግቢያ ላይ ወደሚወስደው መንገድ ላይ በስልክ ሲያወራ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ይህም በሐምሌ ወር በዶሃ በሁለቱ ወገኖች የተፈረሙትን መርሆዎች እንዲሁም ባለፈው ወር በተመሳሳይ ከተማ የተኩስ አቁም ስምምነትን በመከታተል ላይ በተደረገ ስምምነት ላይ የተመሠረተ ነው።

ከዚያ በፊት በሰኔ ወር በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ መካከል በዋሽንግተን በተደረገው ድርድር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ድንቅ ድል" ብለው የጠሩትን የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ አድርገዋል። ነገር ግን ስምምነቱ በተፋላሚ ወገኖቹ ወድያውኑ ተጥሷል።

ኤም23 በዚህ ግጭት ውስጥ ካሉት ትላልቅ ተሳታፊዎች አንዱ ቢሆንም፣ በአሜሪካ የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ በቀጥታ አልተሳተፈም። ቡድኑ የግጭቱን "ዋና መንስኤዎች" ይፈታሉ በሚል በኳታር አሸማጋይነት ተደረጉትን ንግግሮች ይደግፋል።

በጥር ወር የኤም23 አማፂያን የክልሉን ዋና ከተማ ጎማን፣ የቡካቩ ከተማን እና ሁለት አየር ማረፊያዎችን ጨምሮ የምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ትላልቅ ክፍሎች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የአስርት ዓመታቱ ግጭት ተባብሷል።

ከጥር ወር ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

የኪኒሻሳ መንግሥት የምሥራቃዊ የአገሪቱን ክፍሎች በኤም 23 ከተነጠቀ በኋላ ለእርዳታ ፊቱን ወደ አሜሪካ አዙሯል።

ከአሜሪካ በሚያገኘው የደህንነት ዋስትናዎች ምትክ ወሳኝ ማዕድናትን የመጠቀም መብት ለዋሽንግተን እንደሰጠ ተዘግቧል።

ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ በሆኑ ኮልታን እና ሌሎች ሀብቶች የበለፀገች ናት።

ሩዋንዳ ከፍተኛ ማስረጃ ቢኖርም ኤም23ን ትደግፋለች መባሉን ታስተባብላለች። ወታደሮቿ በአካባቢው የተሰማሩት ራሷን እንደ ኤፍዲኤልአር ካሉ የታጠቁ ቡድኖች ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች ለመከላከል መሆኑን አጥብቃ ትገልጻለች።