ኢሰመጉ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, SM
ለባለፉት 33 ዓመት ስራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል እና ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስሥልጣን መታገዳቸውን አስታወቁ።
ሁለቱም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ በተጻፈ ደብዳቤ "ከማንኛውም እንቅስቃሴዎች" መታገዳቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ሐሙስ ታህሳስ 17 ለቢቢሲ በላከው መግለጫ፤ "በታህሳስ 16 [2017] በደረሰን ደብዳቤ ድርጅታችን ከማንኛውም እንቅስቃሴዎች እገዳ እንደተጣለበት ተገልጾልናል" ብሏል።
ኢሰመጉም እገዳው የተላለፈበት በተመሳሳይ ቀን በተላከ ደብዳቤ መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል። ነገር ግን ሁለቱም ድርጅቶች የታገዱበት ደብዳቤ የተጻፈው በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ታህሳስ 14/ 2017 ዓ.ም መሆኑን አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ በጻፈው ደብዳቤ "ድርጅቶቹ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀሳቸው፣ ገለልተኛ አለመሆናቸው፣ ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው መሆኑ" ለእገዳው በምክንያትነት የተጠቀሱ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም "[ድርጅቱ] ሃላፊነት በጎደለው መልኩ የተንቀሳቀሰ መሆኑ በተደረገ ክትትልና ግምገማ ለማረጋገጥ ተችሏል" ሲል ባለሥልጣኑ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አትቷል።
እንደ ማዕከሉ ሁሉ ኢሰመጉም "ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀስ፣ ገለልተኛ አለመሆን፣ የአስተዳደር ወጭ ገደብ ጠብቆ አለመስራት እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ መንቀሳቀስ" የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።
ነገር ግን ሁለቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በባለሥልጣኑ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በመግለጫው "ድርጅታችን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ በየትኛውም ያልተገባ ወይም ከህግ የሚጻረር እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የማያውቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን" ብሏል።
ስራዎቹንም "በፍጹም ገለልተኝነት" ሲሰራ እንደቆየ የጠቀሰው ማዕከሉ፤ "ድርጅታችን ቦርድ መር የሆነ እና ግልጽ አደረጃጀት መዋቅር ኖሮት ለዓመታት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ያለ ነው" ሲል አክሏል።
በተጨማሪም ድርጅቱ "በማያውቀው መልኩ" ሃሳቡ "በሕግ አግባብ ባልተጠየቀበት" ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ክትትል እና ግምገማ ያካሄደ መሆኑን በመግለጽ ያስተላለፈው እገዳ "አግባብነት ያለው እና ህግን የተከተለ ነው" ብሎ እንደማያምን በመግለጫው ጠቁሟል።
በእግዱ ላይ "በቂ ማብራሪያ" እንዲሰጠው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለባለስልጣኑ ማስገባቱን ማዕከሉ ጠቁሟል። ባለሥልጣኑ ይህንን ደብዳቤ ተመልክቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስም ድርጅቱ ከየትኛውም ሥራዎቹ መታገዱን እና ጽህፈት ቤቱም መዘጋቱን ድርጅቱ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
የሰብዓዊ መብቶቹ ላይ ስራዎችን የሚሰራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት በ2013 ዓ.ም. የተመሰረተ ነው።
ኢሰመጉ በባለፉት 33 ዓመታት "በሃገሪቱ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ከፍተኛ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ አንጋፋ ድርጅት" መሆኑን አስታውሷል።
ተቋሙ " ህግና ስርዓትን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ ነጻና ገለልተኛ" ድርጅት መሆኑን በመግለጫው ጠቅሶ ዕግዱ በሚነሳበት ሁኔታ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመነጋገር ላይ ይገኛል ብሏል።
ማዕከላቱ ላይ የተላለፈው እግድ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለእግድ ተዳርገው የነበሩ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን ቁጥር ወደ አራት አድርጎታል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በኅዳር ወር በቀናት ልዩነት ውስጥ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተባሉት ድርጅቶች ላይ እገዳ አስተላልፎ ነበር።
ድርጅቶቹ ላይ የተላለፈው እገዳ ከተነሳ ከጥቂት ቀናት በኋላ፤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች በድጋሜ ታግደዋል።
የድርጅቶቹን ድጋሚ መታገድ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባለፈው ሳምንት አርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ማዕከሉ በዚህ መግለጫው፤ "መንግሥት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሲቪክ ምህዳሩን እንዲጠብቁ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚያደርጉትንም ጥረት እንዲደግፉ እንጠይቃለን።
በተጨማሪም፣ ለሁለቱ ድርጅቶች መዘጋት ዋነኛ ምክንያቶች የሆኑት ነገሮች በበቂ ማስረጃ በተደገፈ መልኩ በግልጽ ለማህበረሰቡ ይፋ እንዲደረጉ እንጠይቃለን" ብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ "የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ ተቋም አሠራርን መፈተሽ ያስፈልጋል። እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው" ብለው ነበር።
ዐቢይ አክለውም "ሰብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው። ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ያስደነገጠ ነበር።
በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመሩ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር "አሳሳቢ" እና "አስደንጋጭ" መሆኑን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።












