የዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛ 'ካሲ' ያልተሰሙ ምስክርነቶችን ለፍርድ ቤት ተናገረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካዊው ራፐር ሾን 'ዲዲ' ኮምብስ የፍርድ ሒደት የመጀመሪያው ሳምንት ላይ የቀድሞው ፍቅረኛው የሰጠችው ምስክርነት አነጋጋሪ ሆኗል።
የአርኤንድቢ ሙዚቀኛዋ ካሳንድራ 'ካሲ' ቬንቱራ ለአራት ቀናት ምስክርነቷን ሰጥታለች። ለዓመታት ይደበድባት እንደነበር በፍርድ ቤት በስሜት ተሞልታ ተናግራለች። በወሲብ ንግድ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር ዕፅ በመጠቀም ይፈጽም የነበረው ወሲብም ገልጻለች።
ለአሥርታት በዚህ የስቃይ ሕይወት ውስጥ መቆየቷን ካሲ ተናግራለች።
"በሐዘን የተሞላ" ሲሉ ምስክርነቷን በፍርድ ቤት የተከታተሉ ገልጸውታል። ዲዲ ጥቃት አድራሽ እና በዝባዥ ብቻ ሳይሆን የወሲብ ወንጀል መረብ የዘረጋም ነው ተብሏል።
በማንሀተን ፍርድ ቤት ካሲ ቃሏን ስትሰጥ ሁሉም ሰው በአንክሮ እያዳመጠ ነበር። የስምንት ወር ነፍሰ ጡሯ ሙዚቀኛ በዐቃቤ ሕግ ምስክርነት እንድትሰጥ ተጠይቃለች።
የቀድሞ ፍቅረኛዋ ዲዲን ለስድስት ዓመታት አላገኘችውም።
ዲዲ ከሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ እና ዝውውር ጋር የተያያዙ ክሶች ተመሥርተውበታል። ካሲንም ይበዘብዛት እንደነር በፍርድ ቤት ቃሏን ሰጥታለች።
በማትፈልገው የወሲብ ድርጊት ውስጥ ያስገባት እንደነበርም ገልጻለች።
ለ11 ዓመት ተኩል አብራው ስትቆይ "freak-offs" በመባል የሚታወቁ የወሲብ ክንውኖችን በማዘጋጀት ካሲንም ያሳትፋት እንደነበር ተናግራለች።
በወሲብ ብዝበዛ፣ በመመሳጠር እና ለወሲብ ንግድ ሰዎችን በማዘዋወርም ተከሷል። ዲዲ ግን ክሶቹን አስተባብሏል።
ዲዲ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ልጆቹ እና ጓደኞቹም ተገኝተዋል።
ዳኛ አሩን ሰብራማኒን ዐቃቤ ሕጎች ምስክራቸውን እንዲያቀርቡ ሲጠይቁ ካሲ ምጧ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።
ሙዚቀኛዋ ገናና ከሆነው ራፐር ጋር በፍቅር መውደቋን ታስታውሳለች።
ስታገኘው ገና 19 ዓመቷ ነበር። ዲዲ በ17 ዓመት ይበልጣታል። የሙዚቃ ሪከርድ ሌብሊ ውስጥ አስገባት።
ተዋውቀው ብዙም ሳይቆዩ ግንኙነታቸው ተጀመረ። ዲዲ ሌላ አደገኛ ገጽታ እንዳለው ያወቀችው ያኔ ነው።
ምስክርነቷን ስትሰጥ እያለቀሰች ነበር። ዲዲ መላው ሕይወቷን ለመቆጣጠር ይሞክር እንደነበር ተናግራለች።
ለመኪና፣ ለቤት ኪራይ፣ ለስልክ ገንዘብ ይከፍልላት እንደነበር እና ሲበሳጭ ግን "ለቅጣት" ብሎ መክፈል ያቆም እንደነበር ገልጻለች።
አንድ ቀን ተኝታ ስለነበር እንደመታት እና ሽፋሽፍቷ እንደተሰነጠቀ አስታውሳለች። ሁለት ጓደኞቹ ሊያስቆሙት ቢሞክሩም ከአልጋ ጋር አጋጭቷታል።
በምሥጢር የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ቆዳዋን እንዲጠግን መቅጠሩንም ለፍርድ ቤት ተናግራለች።
በአንድ ፓርቲ ላይ ከሽንት ቤት መቀመጫ ጋር አጋጭቶ እንደደበደባትም ካሲ ምስክርነቷን ሰጥታለች።
ምስክርነቷን ስትሰጥ ምሥሎች እና ቪድዮዎች የታዩ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቱ የሚያለቅሱ ሰዎችም ነበሩ።
አምና ሲኤንኤን ያወጣው ቪድዮ ዲዲ ካሲን እአአ በ2016 በሎስ አንጀለስ ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ሲደበድባት ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቱት ይህ ቪድዮ በፍርድ ቤትም በማስረጃነት ቀርቧል።
ዲዲ የሚያዘጋቸውን የወሲብ ክንውን ጥላ ለመውጣት በመሞከሯ ድብደባውን እንደፈጸመባትም ካሲ ገልጻለች።
በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሁለት ወንዶችን ቀጥሮ ከካሲ ጋር ወሲብ ሲፈጽሙ ዲዲ ይቀርጽ ነበር።
የፍቅር ግንኙነታቸው በተጀመረ በሁለተኛው ዓመት እነዚህ የወሲብ ድርጊቶች ውስጥ ያካትታት እንደጀመረ ተናግራለች ።
እሱን ደስተኛ ለማድረግ ስትል ብትሳተፍም በጊዜ ሒደት ግን እሷ ላይ የሚደርሰው ውርደት እየጨመረ ሄዷል።
እነዚህ ድርጊቶች እስከ አራት ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ። እንቅልፍ እንዳይወስዳት መድኃኒት መውሰድም ነበረባት። የማህጸን ኢንፌክሽንን ጨምሮ የተለያዩ ህመሞች እንደገጠሟት እና በአንድ ወቅት ወደ መታጠቢያ ቤት ስትሄድ ራሷን መሳቷን ገልጻለች።
"ይህ ፍሪክ-ኦፍስ የወሲብ ክንውን ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር። እንደ ሥራ ሆኖ ነበር። ከዚህ ክንውን ለማገገም መሞከር የተለመደ ነገር ሆኖም ነበር" ብላለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የወሲብ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጻለች።
ዲዲ ከሌሎች ሴቶች ጋር ግንኙነት በማድረጉ በተደጋጋሚ ቢለያዩም በስተመጨረሻ በ2018 ግንኙነቱን አቋርጣለች።
በ2018 ቤቷ ውስጥ ሳለች ዲዲ እንደደፈራት በፍርድ ቤት እያለቀሰች ቃሏን ሰጥታለች።
አሁን ከግል አሠልጣኟ አሌክስ ፋይን ጋር ትዳር መሥርተው ሁለት ልጆች አፍርተዋል።
ሆኖም ከዲዲ ጋር ሳለች የደረሰባት ስቃይ አሁንም ድረስ ጠባሳው እንዳለ ተናግራለች።
ጠባሳው እንቅልፍ ሲነሳት ከሁለት ዓመት በፊት ራሷን ለማጥፋት ሞክራ ባለቤቷ የሥነ ልቦና አማካሪ ጋር እንዳገናኛት ተናግራለች።
ዐቃቤ ሕግ የካሲን ምስክርነት ዲዲ ከተከሰሰበት ሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ እና ዝውውር ጋር እያስተሳሰረ ነበር።
የዲዲ ጠበቃ ዲዲ በዝባዥ እንደነበር እንደማይክዱ እና በቤት ውስጥ ጥቃት ክስ ሊመሠረትበት እንደሚችል ገልጸዋል።
"የቤት ውስጥ ጥቃት የወሲብ ንግድ አይደለም" ሲሉ ጠበቃው ቴኑ ግሪጎስ ተከራክረዋል።
የፌደራል መንግሥት ክስ ለወሲብ ንግድ ሰዎችን ማዘዋወር እና የወሲብ ንግድ ሰንሰለት መዘርጋትን እና የተቀናጀ የወንጀል መረብ ለመዘርጋት መመሳጠርን ይጨምራል።
ተባባሪ ዐቃቤ ሕግ ኤምሊ ጆንሰን እንዳሉት የካሲ ምስክርነት ክሱን ለማጠናከር ይረዳል።
ዲዲ መሣሪያዎች እንደሚያገኝ እና እሷንም ምሥጢር እንድትጠብቅ ያስገድዳት እንደነበር ተናግራለች።
ካሲ "ካስቸገረች" የተቀረጹ የወሲብ ቪድዮዎችን እንደሚለቃቸው ያስፈራራት እንደነበርም በፍርድ ቤት ተናግራለች።
"አጣብቂኝ ውስጥ ነበርኩ" ብላለች።
በክሱ ላይ ስሟ ያልተጠቀሰ ከሳሽን የወከሉት ጠበቃ አሪክ ፉዳሊ እንዳሉት ከሳሿ "ከተናገረች ምን እንደሚገጥማት በመፍራት" ማንነቷን መደበቋን ገልጸዋል።
"አንድ ሰው በፈቃዱ ወሲብ ሊፈጽም ይችላል። ተገድዶ ፈቃዱን እንዲሰጥ ሊደረግም ይችላል" ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት የካሲን ምስክርነት በመጠቀም ክሱን እንደሚያደራጅ ተገልጿል።
የካሲ ጠበቃ አና ኤስተቮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የስልክ መልዕክት ልውውጦችን በማስረጃነት አቅርበዋል።
ግንኙነታቸው በአደንዛዥ ዕፅ እና በብዝበዛ የተሞላ እንደነበር ካሲ ተናግራለች።















