ኮሎምቢያ ጀልባዋ ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ አሜሪካ ላይ የግድያ ክስ አቀረበች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በአገሪቱ የውሃ ክልል ላይ ባለፈው መስከረም በጀልባ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ አሜሪካ "ግድያ" ፈፅማለች ሲሉ ከሰሱ።
ፕሬዝዳንት ፔትሮ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አሜሪካ የአገራቸውን ሉዓላዊነት መጣሷን ገልጸው፣ ኮሎምቢያዊያን የአሳ አስጋሪዎች ገድላለች ሲሉ ወንጅለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገፃቸው ጀልባው ላይ ጥቃት ሲፈፀም "የኮሎምቢያው ጀልባ የሞተር ብልሽት ስለገጠመው የአደጋ ምልክት አብርቶ ነበር" ብለዋል።
"ከአሜሪካ መንግሥት ማብራሪያ እየጠበቅን ነው" ሲሉም አክለዋል።
የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት ባለፈው ሐሙስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ "ዕፅ የጫነ ሰርጓጅ መርከብ" ላይ ጥቃት መፈፀሟን እና ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው።
ትራምፕ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ጀልባው "በአብዛኛው ፌንትኔል እና ሌሎች ሕገ ወጥ ዕፆችን የጫነ" መሆኑ እንደተረጋገጠ ተናግረዋል።
ጥቃቱ በቅርብ ሳምንታት በካሪቢያን ባሕር አሜሪካ ጀልባዎች ላይ የፈፀመችው ስድስተኛው ነው። ከጥቃቱ ሰዎች መትረፋቸው ሲነገር ደግሞ ይህ የመጀመሪያው ነው።
እሁድ ዕለት መስከረም ስለተፈፀመው ጥቃት አስተያየት የሰጡት ፕሬዝዳንት ፔትሮ "የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ፈፅመዋል እና የአገራችንን የውሃ ግዛት ሉዓላዊነት ጥሰዋል" ብለዋል።
"አሳ አስጋሪ አሊሃንድሮ ካራንዛ ከዕፅ ንግድ ጋር ምንም ትስስር የለውም እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው አሳ ማውጣት ነው። የኮሎምቢያ ጀልባው እየተንሳፈፈ ነበር፤ በሞተር ብልሽት ምክንያት የአደጋ ጊዜ ጥሪውን አብርቶ ነበር።"
አሊሃንድሮ ካራንዛ እ.አ.አ መስከረም 15 በካሪቢያን ባሕር አሳ እያሰገረ እያለ ጀልባው ላይ በአሜሪካ ኃይሎች ተከፈተበት በተባለ ተኩስ እንደተገደለ ተነግሯል።
ትራምፕ የቀጠለውን የጀልባ ጥቃት በመደገፍ፤ ከላቲን አሜሪካ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እየጎረፈ ያለውን ዕፅ የመከላከል ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥታቸው የጀልባዎቹን እና የተሳፋሪዎችን ማንነት የሚገልፅ ማስረጃም ሆነ ዝርዝር መረጃ ይፋ አላደረገም።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተሾሙ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የአሜሪካን ጥቃቶች "ያለ ፍርድ ግድያ" ሲሉ ገልፀውታል።
ከዚህ ቀደም በቬንዙዌላ አቅራቢያ በተፈፀሙ አምስት የጀልባ ጥቃቶች ቢያንስ 27 ሰዎች መገደላቸውን ከአሜሪካ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ትራምፕ ትሩዝ በተባለው ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው በቅርቡ ጥቃት የደረሰበት መርከብ "ግዙፍ መጠን ያለው ዕፅ ለማጓጓዝ ሲባል የተገነባ ነው" ብለዋል።
"እነዚህ ንፁሃን ሰዎች አይደሉም። ሰርጓጅ መርከብ ያላቸው ብዙ ሰዎች አላውቅም። እናም ጥቃቱ የተፈፀመው ዕፅ የያዘ፣ የጫነ ሰርጓጅ መርከብ ላይ ነው" በማለት የአሜሪካ ጦር ወታደሮችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልፀዋል።
ከጥቃቱ የተረፉ ሁለት ሰዎች ወደ ትውልድ አገራቸው ኢኳዶር እና ኮሎምቢያ እንደሚመለሱም አክለው ተናግረዋል።
ትራምፕ ባለፉት ሳምንታት ዕፅ ወደ አሜሪካ ይልካሉ ባሉት የቬንዙዌላ አስተዳደር ላይ ዛቻቸውን አጠናክረዋል።
የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማድሮ ትራምፕ የደቡብ አሜሪካዊቷን አገር "የአሜሪካ ግዛት" ለማድረግ እየሞከሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።















