የእሑድ የዝውውር ጭምጭምታዎች፡ ፖቸቲኖ፣ ማውንት፣ ማክ አሊስተር፣ ዎከር፣ ኦናና፣ ኔቭስ እና ቤሊንግሃም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የቶተንሃም ሆትስፐር እና የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ በክረምቱ የቼልሲ አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ቴሌግራፍ ዘግቧል።
እንደሜይል ዘገባ ከሆነ ደግሞ ፖቸቲኖ አማካዩ ሜሰን ማውንትን በስታምፎርድ ብሪጅ እንዲቆይ ይፈልጋሉ። የ24 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ ውል አንድ ዓመት ብቻ ቢቀረውም እንዲያራዝም ጥያቄ አልቀረበለትም።
ሊቨርፑል 70 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ የወጣለትን የዓለም ዋንጫ አሸናፊው አሌክሲስ ማክ አሊስተርን ለማስፈረም የሚያደርገውን ጥረት ማቋረጡን ሚረር ዘግቧል።
ቼልሲ በክረምቱ የብራይተን እና የኢኳዶር አማካይ ሞዬስ ካይሴዶን በእጁ ለማስገባት 70 ሚሊዮን ፓውንድ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ተብሏል።
የ32 ዓመቱ የማንቸስተር ሲቲ እና እንግሊዝ ተከላካይ ካይል ዎከር ከአገሩ ውጪ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራቱን በኢትሃድ ስታዲየም ለመጨረስ ማቀዱን ሰን ዘግቧል።
በሌላ የሰን ዘገባ የማንቸስተር ዩናይትድ የባለቤትነት ጉዳይ እልባት ካገኘ በኋላ ለ25 ዓመቱ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።
ኤቨርተኖች ከፕሪምየር ሊግ የሚወርዱ ከሆነ ቤልጂየማዊው አማዱ ኦናናን ለመውሰድ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ለሚያቀርብ ለመሸጥ ፈቃደኛ መሆናቸው ታውቋል።
ባርሴሎናዎች የ26 ዓመቱን የዎልቭስ አማካይ ሩበን ኔቭስን የማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው ቶክስፖርት ዘግቧል።
እንግሊዛዊው አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም ከቦርሲያ ዶርትመንድ ወደ ማንቸስተር ሲቲ እንዲዘዋወር የቀረበለትን ጥያቄ 'ፕላስቲኩን ክለብ’ መቀላቀል ስላልፈለገ ውድቅ ማድረጉ ተዘግቧል።
በበርሚንግሃም የሚጫወተው የቤሊንግሃም ታናሽ ወንድም ጆብ ወደ ሰንደርላንድ ለመዘዋወር እየተቃረበ ነው ተብሏል። በስታዲየም ኦፍ ላይት ተገኝቶ ሰንደርላንድ ያደረገውን ጨዋታ ቅዳሜ ዕለት መከታተሉም ታውቋል።
አስቶንቪላ የ27 ዓመቱን የሪያል ማድሪድ አማካይ ማርኮ አሴንሲዮን እና የ23 ዓመቱን የባርሴሎና አጥቂ ፌራን ቶሬስን ለማስፈረም ይፈልጋል ተብሏል።
ቶሬስ በባርሴሎና መቆየት እንደሚፈልግ እና ከቪላ ጋር ምንም ግንኙነት እንዳልነበረው ተናግሯል።
ሪያል ማድሪድ ፈረንሳዊውን ፌርላንድ ሜንዲን ሊሸጥ እንደሚፈልግ ሲገለጽ አርሰናል ፍላጎትማሳየቱ ተዘግቧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የባየር ሙኒኩን አማካይ ሪያን ግራቨንበርችን በዚህ ክረምት ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱ ታውቋል።
የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል ፕሬዝዳንት ፋሃድ ቢን ሳድ ቢን ናፍል ቡድናቸው አርጀንቲናዊውን አጥቂ ሊዮኔል ሜሲን ሊያስፈርም ይፈልጋል ስለሚባለው ጉዳይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
እንደ ማርካ ዘገባ ደግሞ አትሌቲኮ ማድሪድ የመሃል ተከላካዩን ሳንቲያጎ ሞሪኖን ከሬሲንግ ክለብ ዴ ሞንቴቪዴዮ ለማስፈረም እየተነጋገረ ነው።
ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የ18 ዓመቱ የሊቨርፑል ተከላካይ አይዛክ ማባያ ከክለቡ ጋር አዲስ ኮንትራት ተፈራርሟል።
ማንቸስተር ሲቲ የ15 ዓመቱን ግብ ጠባቂ ስፒክ ብሪትስን ከኤኤፍሲ ዊምብልደን ለማስፈረም ከጫፍ መድረሱን ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዘግቧል።












