በ5 የዓለም ዋንጫዎች በመሳተፍ የመጀመሪያ የሆኑት እግርኳስ ተጫዋች በ93 አመታቸው አረፉ

ሜክሲኳዊው አንቶኒዮ ካርባጃል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ የመጀመሪያ የሆኑት እግር ኳስ ተጫዋች ሜክሲኳዊው አንቶኒዮ ካርባጃል በ93 ዓመታቸው አረፉ።

‘ላ ቶታ’ በመባል የሚታወቁት እኚህ ግብ ጠባቂ በብራዚል በ1950፣ በስዊዘርላንድ በ1954፣ በስዊድን 1958፣ በቺሊ 1962 እና በእንግሊዝ በ1966 በተዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተጫውተዋል።

ካራባጃል ለ32 ዓመታት ያህልም ክብረ ወሰኑን ይዘው የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1998 ጀርመናዊው ሎታር ማታውስ አምስት ጊዜ በዓለም ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ ተጋርተውታል።

ግብ ጠባቂው ለሃገራቸው ሜክሲኮ 48 ጨዋታዎችን ያሸነፉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 11 በዓለም ዋንጫዎች ነው። በክለብ ደረጃም 409 ጨዋታዎችን ተጫውተዋል።

አብዛኛውን የ18 ዓመት የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወታቸውን ያሳለፉት በሜክሲኮው ክለብ ሊዮን ሲሆን በዚህም ክለብ ለ16 ዓመታት ያህል ተጫውተው፣ 364 ጨዋታዎችን አካሂደዋል።

በእግር ኳስ ስኬታቸው ምክንያት በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ‘ኤል ሲንኮ ከፓስ’ እየተባሉ ለሚጠሩት ካርባጃልም አክብሮት ለመግለጽ የቀድሞ ክለባቸው ሀሙስ ዕለት የስታዲየሙን በሮች ክፍት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

“ዶን አንቶኒዮ፤ ታላላቆች አይሞቱም” ሲል ክለቡ ለእግር ኳስ ተጫዋቹ ያለውን አክብሮት ገልጿል።

“ሁልጊዜም ፈለግህን እንከተላለን። የቡድንህ አካል መሆን ለኛ ክብራችን ነው” ሲልም አክሏል።

ክለቡ ለደጋፊዎቹ “በታላቅ ክብርና ፍቅር የኤመራልድን ታላቅ ለመጨረሻ ጊዜ እንሰናበተው” ብሏል።

በአጠቃላይ አምስት የዓለማችን ተጫዋቾች ካርባጃልን በአምስት የዓለም ዋንጫ በመጫወት ካስመዘገቡት ታሪካዊ ስኬት ጋር ተጋርተዋል። ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ የሜክሲኪኮ ተጫዋቾች ናቸው።

የሜክሲኮው አማካኝ አንአንድሬስ ጋርዳዶ ባለፈው አመት በኳታር በነበረው የዓለም ዋንጫ አምስተኛውን ተሳትፎ አድርጓል።

አርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ እና ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንዲሁ በኳታሩ ዋንጫ አምስት ዋንጫዎች መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሌላኛው ሜክሲኳዊ ተጫዋች ራፋኤል ማርኬዝ በአውሮፓውያኑ 2018 ሁለተኛው አምስት ዋንጫዎች ላይ የተሳተፈ ሆኗል።

“በአምስት የፊፋ የአለም ዋንጫዎች በመሳተፍ የመጀመሪያው የሆነውን ኮከብ አንቶኒዮ ካርባጃል ማለፉ ታላቅ ሃዘን ፈጥሮብናል” ሲሉም የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

"ለቤተሰቦቹ እና እሱን በማጣታቸው ሃዘን ላደረባቸው የሜክሲኮ ደጋፊዎች በሙሉ ልባዊ ሀዘንን እገልጻለሁ" ብለዋል።