ኢትዮጵያ በአፍሪካ በርካታ ህጻናት ካለጊዜያቸው ከሚወለዱባቸው አገራት አንዷ ናት ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ ከጊዜያቸው ቀድመው በርካታ ጨቅላ ህጻናት ከሚወለዱባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት በጋራ ያወጡት አዲስ ሪፖርት አመለከተ።
በዚህ ሪፖርት መሠረት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አይቮሪ ኮስት በርካታ ህጻናት ካለጊዜያቸው የሚወለዱባቸው አገራት ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ - ዩኒሴፍ እና በእናቶች እና በጨቅላ ህጻናት ጤና ላይ የሚሰራ ድርጅት በጋራ ያወጡት ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ከተገቢው ጊዜ ቀድመው የሚወለዱ ልጆች ላይ የሚያጋጥመው ሞት፣ በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱ የጨቅላ ህጻናት ሞት ቀዳሚው ምክንያት ነው።
ይህም ከአምስት ህጻናት ከአንድ በላይ የሚሆኑት አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ለሞት ለሚዳረጉ ሁሉም ህጻናት ህልፈት ይኸው ያለጊዜ ቀድሞ መወለድ ሰበብ እንደሆነ ተገልጿል።
በአብዛኛው ካለጊዜያቸው የተወለዱ ጨቅላ ህጻናት በሕይወት ለመቆየት በሕክምና ተቋማት ውስጥ መወለዳቸው ወሳኝ ነው ብሏል ሪፖርቱ።
በዓለም ዙሪያ ከሚወለዱ 10 ህጻናት መካከል አንዱ ከተገቢው ጊዜ ቀድሞ ይወለዳል። ከእነዚህም መካከል በየ40 ሰከንዱ አንዱ ለህልፈት ይዳረጋል።
ይህ ህጻናት ካለጊዜ የመወለድ ሁኔታ ምን ያህል በስፋት እንደሚከሰት ያሳየው አዲስ መረጃ የተሰባሰበው በዓለም ጤና ድርጅት እና በዩኒሴፍ አማካይነት በለንደኑ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሲን ትምህርት ቤት አማካይነት ነው።
ሪፖርቱ ጨምሮም ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ካለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት መጠን በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ለውጥ አላሳየም ብሏል። ከአውሮፓውያኑ 2010 አስከ 2022 ድረስ ባሉት 10 ዓመታት ቢያንስ 152 ሚሊዮን ህጻናት ካለጊዜያቸው ተወልደዋል።
“በአሁኑ ጊዜ ዝም የምንልበት ምክንያት የለም። ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑት ጨቅላ ህጻናቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመለወጥ መሣሪያው እና ዕውቀቱ አለን” በማለት የሪፖርቱ ተባባሪ አዘጋጅ የታንዛኒያው ዶክተር ናህያ ሳሊም ተናግረዋል።
ጨቅላ ህጻናት ከጊዜያቸው ቀድመው ተወልደዋል የሚባሉት እርግዝናው ከተፈጠረ ከ37 ሳምንታት ቀድመው የተወለዱ እንደሆነ ነው። መደበኛው የእርግዝና ጊዜ 40 ሳምንታት ያህል ይሆናል።
እናቶች ከተገቢው ጊዜ ቀድመው እንዲወልዱ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ የቀደመ ያለጊዜ ወሊድ እና ከአንድ በላይ ጽንስ መኖር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
ካለጊዜያቸው የሚወለዱ ጨቅላዎች ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ያልዳበረ ሳምባ፣ የሰውነት ሙቀትን መቆጣጠር አለመቻል፣ ዝቅተኛ የምግብ ፍላጎት እና ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ይሆናሉ።
ካለጊዜያቸው የተወለዱ ጨቅላዎች ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ወይም ጥብቅ የህጻናት ጤና እንክብካቤ፣ መድኃኒት እንዲሁም አንዳንድ ጊዜም የቀዶ ህክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል።












