ኢራን የተቃውሞ ሰልፍ ደግፏል ባለችው ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቿ ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች

አሊ ካሪሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሊ ካሪሚ በኢራን የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ደግፈው ከተናገሩ ዝነኛ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ኢራን በእግር ኳሱ ኮከብ አሊ ካሪሚ፣ ባለቤቱ እና ቤተሰቦቿ ላይ የጉዞ እገዳ መጣሏን ቢቢሲ የተመለከተው ሾልኮ የወጣ ሰነድ አመለከተ።

የጉዞ እገዳው የተጣለው በቅርቡ በአገሪቷ በተካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ወቅት ነው።

ካሪሚ መስከረም ወር ላይ የተቀሰቀሰውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ከደገፉ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር።

‘የእስያው ማራዶና’ በመባል የሚታወቀው እግር ኳስ ተጫዋቹ በተቃውሞው ወቅት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይኖር ነበር።

ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ኩርዳዊት ኢራናዊ ሴት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ ነበር።

የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በሥነ ምግባር ፖሊስ ከታሰረች በኋላ በተፈፀመባት ድብደባ ሕይወቷ እንዳለፈ ይታመናል።

ይህንንም ተከትሎ በመላ አገሪቷ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን መንግሥት በወሰደው የኃይል እርምጃ ተቃውሞው ሊታፈን ችሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት ተቃውሞው ከጀመረ አንስቶ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ 70 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 530 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ፐርዢያ ከተመለከታቸው ሰነዶች አንዱ፣ “ካሪሚ ወደ ኢራን እንዲመጣ በወኪላችን ዘጠኝ ጊዜ ግብዣ የቀረበለት ሲሆን በዚህም ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ደርሶናል” ይላል።

ከፍተኛ ምስጢር በሚል ምልክት የተደረገበትና የኢራን አብዮት ጠባቂ የደኅንነት ክፍል በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 24/2022 የጻፈው ደብዳቤ “የካሪሚ የቅርብ ጊዜ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በባለቤቱ ሳሃር ዳቫሪ እና በቤተሰቧ የተነሳሱ ናቸው” ሲል ለአቃቤ ሕግ አሳውቋል።

ኢራን በ1980ዎቹ መጨረሻ የኮሚኒስት ቱደህ ፓርቲ አባል ናቸው በሚል ክስ የካሪሚን ባለቤት አባት ጎላማሊ ዳቫሪን በሞት ቀጥታለች። ጎላማሊ በዚያን ወቅት በኢራን አየር ኃይል መኮንን ነበሩ።

የካሪሚ አማቶች በቋሚነት ለመሰደድ እሱን ወክለው በዋና ከተማዋ ቴህራን ግዛት፣ ላቫሳን የሚገኘውን ግዙፍና ቅንጡ መኖሪያ ቤቱን በ20 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ አቅደው እንደነበርም ደብዳቤው ያስረዳል።

በዚህም አብዮታዊ ጥበቃው በካሪሚ ፣ በባለቤቱ፣ በእናቷ፣ በእንጀራ አባቷ፣ በወንድም እና እህቷ ላይ የጉዞ እገዳ እንዲጣል ጠይቋል።

ይህም ካሪሚ አሊያም ሚስቱ ወደ አገሪቷ ከገቡ፣መልሰው መውጣት እንዳይችሉ ይከለክላል።

ቢቢሲ ሾልኮ የወጣውን ይህን ሰነድ ያገኘው ከመረጃ ሰርሳሪ ቡድኑ ኢዳላት ኢ አሊ(ኢሊስ ጀስቲስ) ነው።

ካሪሚ ከቢቢሲ ፐርዢያ ጋር በስልክ ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደተናገረው ታላቅ ወንድሙም ብዙ ጊዜ የተከሰሰ ሲሆን ከአገር እንዳይወጣም ተከልክሏል።

ከዚህም በተጨማሪ “ ጓደኛዬ ለሦስት ወይም ለአራት ጊዜ ያህል በኢቪን እስር ቤት ተወስዶ በጸጥታ ኃይሎች ተጠይቋል” ብሏል።

ካሪሚ እንደሚለው ኢራን በኢንስታግራም የሚከተላቸው ሰዎች ላይም የቅርብ ክትትል ታደርጋለች።

“ከመካከላቸው አንዳቸውም ኢራንን ለቀው ለመውጣት ተቀማጭ ገንዘብና ዋስ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል” ብሏል።

ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ካሪሚ በላቫሳን የሚገኘውን መኖሪያ ቤቱን እንደሸጠ ዘግቦ ነበር።ካሪም ግን ዜናው ሀሰት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ የጸጥታ ኃይሎች ቦታውን በመውረር ንብረቱን የሚቆጣጠርለት ሠራተኛውን በጭካኔ ደብድበዋል” ሲልም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቤቱ ማንም እንደሌለበት ጨምሮ ተናግሯል።

“አንዳንድ ምሽቶች መብራት እንደሚበራ እና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎች ሲገቡ እና ሲወጡ እንደሚመለከቱ ጎረቤቶቼ ነግረውኛል” ብሏል ካሪሚ።

ካሪሚ የኢራን ባለሥልጣናት ቤቱ አቅራቢያ የገጠሙትን የደኅንነት ካሜራ ምስልም አጋርቷል።

“ ማንኛውም መኪና በአካባቢው ለአምስት ደቂቃ ያህል ከቆመ፣ የጸጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው ይጎርፋሉ” ብሏል።

አሁን ላይ ካሪሚ እና ቤተሰቦቹ ይኖሩበት ከነበረው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይፋ ወዳልተደረገ ሌላ ቦታ ሄደዋል።