የተመድ ማዕቀብ የተመለሰባት ኢራን ውጥረቶችን እንዳታባብስ ሦስት የአውሮፓ አገራት አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት አንስቶት የነበረው ማዕቀብ በድጋሜ መመለሱን ተከትሎ ኢራን ውጥረቱን እንዳታባብስ እና ድርድር እንድትቀጥል ዩናይትድ ኪንግደም፣ፈረንሳይ እና ጀርመን ጥሪ አቀረቡ።
በኢራን ላይ ማዕቀቡን በድጋሜ የጣሉት ሦስቱ አገራት፣ኢራን ከኒውክሌር ኃይሏ ጋር ተያይዞ ባለው ውጥረት ምክንያት እና ለዚህም ትብብር ባለማሳየቷ ማዕቀቡን ከመመለስ ውጭ ምንም ምርጫ እንዳልነበራቸውና የመጨረሻው አማራጫቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ " ኢራን ውጥረቱን ከሚያባብስ ድርጊት እንድትታቀብ እናሳስባለን" ያሉ ሲሆን የተመድን ማዕቀብ እንደገና መመለስ የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማብቂያ አይደለም ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢራኑ ፕሬዚደንት ማስዑድ ፔዝሽኪን አገራቸው የኒውክሌር የጦር መሳሪያ የማበልጸግ ፍላጎት እንዳልነበራት ገልጸው ዓለም አቀፉ ማዕቀብ እንደገና መመለሱን " ፍትሃዊ ያልሆነ፣ አድሏዊ እና ሕገ ወጥ" ሲሉ አውግዘውታል።
ተመድ ቅዳሜ እለት ባካሄደው ጉባኤ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ጉልህ የሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ከአስር ዓመት በፊት አንስቶት የነበረውን የኢኮኖሚ እና የጦር ማዕቀቦች ዳግም መልሷል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2016 ኢራን እንድታቆም የተደረገውን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን እንደገና አጠናክራለች በሚል አሜሪካ ከስምምነቱ ወጥታለች።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳዳር ወቅት የተደረሰው የጋራ ሥምምነት "ጉድለት አለበት" ሲሉ በመተቸት ነበር አገራቸው ከሥምምነቱ እንድትወጣ ያደረጉት።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በሦስቱ አገራት እና በኢራን መካከል ውይይት ቢደረግም ማዕቀቡን ሊያዘገይ የሚችል ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies
ኢ3 በመባል የሚጠሩት ሦስቱ የአውሮፓ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እሑድ እለት በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ኢራን በተደጋጋሚ የገባችውን ስምምነት ከጣሰች በኋላ አገራቱ "ምንም ምርጫ እንዳልነበራቸውና ወደ ማዕቀብ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እና ድርድሮችን ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ኢራን "ስጋቶቻቸውን ለመፍታት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን አለመውሰዷን፤ እንዲሁም ምንም እንኳን ንግግር ቢደረግም ማዕቀቡን ለማራዘም የቀረቡላትን ጥያቄዎች አለመቀበሏን" ሚኒስትሮቹ ጠቅሰዋል።
ቴህራን ከተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከሆነው የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ጋር ለመተባበርም አልፈቀደችም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢራን የኒውክሌር ተቆጣጣሪውን መርማሪዎች ወደ የኒውክሌር ጣቢያዎቿ እንዲገቡ አለመፍቀዷን እና በከፍተኛ የዩራኒየም የበለጸገውን ክምችት በተመለከተ ሪፖርት አዘጋጅታም አለማቅረቧን ገልጸዋል።
ሰኔ ወር ላይ እስራኤል እና አሜሪካ በበርካታ የኒውክሌር ጣቢያዎቿ እና የጦር ሰፈሮቿ ላይ የቦምብ ድብደባ ከፈፀሙ በኋላ ኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲን የክትትል ሥራ አግዳለች።
በኒውክሌር ውሉ መሰረት ኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎቿን የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ ለመፍቀድ የምትገደድ ሲሆን አርብ እለትም ኤጀንሲው ክትትላቸውን እንደገና መጀመራቸውን አረጋግጠዋል።
ሆኖም ኢራን መፍትሔ ለመፈለግ ከኤጀንሲው ጋር እየተነጋገረች ባለችበት ወቅት ማዕቀቡ እንደገና መመለሱ የባሰ ውጥረት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቃለች።
ፔዝሽኪንም ቀደም ሲል ኢራንን ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንድታቋርጥ ሲያደርጉት ወደነበረው ዛቻ ተመልሰዋል።
አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ቴህራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ መርሃ ግብሯን መደበኛ ለማድረግ መሠረተ ልማቶቿ በእስራኤል ጥቃት እንደማይፈፀምባቸው ማረጋገጫ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢራን ማዕቀቡን ለሦስት ወር ለማራዘም በሚል የምታበለጽገውን የዩራኒየም ክምችት እንድታቀርብ በአሜሪካ የቀረበውን ጥያቄ " በእንደዚህ ዓይነት ወጥመድ ውስጥ ራሳችንን ለምን እናስገባለን? በየወሩ ለምን ገመድ አንገታችን ላይ እናጠልቃለን? " ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።
ኢራን ቅዳሜ እለት የዩኬ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን አምባሳደሮቿን ለምክክር እንደምትጠራ ገልጻለች።















