የሎስ አንጀለስ ከተማ ለኮቢ ብሪያንት ባለቤት 29 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሎስ አንጀለስ ከተማ ከሁለት ዓመት በፊት ህይወቱ በሄሊኮፕተር አደጋ ለተቀጠፈው ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢ ብሪያንት ባለቤት 29 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።
የከተማዋ አስተዳደር ይህንን ለመክፈል የተስማማው ከሁለት ዓመት በፊት የኮቢን ህይወት የቀጠፈውን አደጋና አሟሟቱን የሚያሳዩ አሰቃቂ ምስሎችን የከተማዋ ፖሊስ በማጋራቱም ነው።
በደረሰው አደጋ ኮቢ ብሪያንት፣ ሴት ልጁ ጂያና እና ሌሎች ሰባት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ባለቤቱ ቫኔሳ ብሪያንት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አስከሬኑን እንደ “ቅርስና” “ጌጣጌጥ” በመቁጠር ፎቶግራፍ አንስተዋቸዋል ስትል ከሳም ነበር።
የሎስ አንጀለስ ከተማ አስተዳደር ጠበቆች በበኩላቸው የተደረሰው ስምምነት “ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ” ብለውታል።
“የዛሬዋ ዕለት በዚህ አሰቃቂ ተግባር የተሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ የቫኔሳ ድፍረት የተሞላበት ትግል ፍጻሜ ያገኘበት” ነው ሲሉም የከሳሿ ጠበቆች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“ለባለቤቷ፣ ለልጇ እንዲሁም በዚህ ተግባር ዝቅ ለተደረጉ ሟች ቤተቦች ሁሉ ታግላለች። በችሎት ላይ ያስገኘችው ድል ለእንደነዚህ ዓይነት ተግባሮች እልባት በመስጠት እንደሚያቆሙት ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
የሎስ አንጀለስ ከተማ አስተዳደርን ወክለው በዋነኝነት የመሩት የህግ ባለሙያ ሚራ ሃሽማል በሰጡት መግለጫ ከአደጋው ጋር የተገናኙ ሙግቶች በሙሉ መቋጫ አግኝቷል ብለዋል።
“ቫኔሳ ብራያንት ሆነ ልጆቿ ከዚህ ጉዳት እንደሚያገግሙ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ሚና ሃሽማል ገልጸዋል።
በዚህ አደጋ ባለቤቱ እና ሴት ልጆቹን ያጣው ክሪስ ቼስተር ከአስተዳደሩ 20 ሚሊዮን ዶላር ለብቻቸው እንደተሰጣቸው ጠበቆች ለአሜሪካ ሚዲያ ተናግረዋል።
ቫኔሳ ለቅርጫት ኳስ ውድድር ለማድረግ ጉዞ ላይ የነበሩትን “የሞቱ ልጆችን አሰቃቂ ፎቶ፣ ወላጆችና የአሰልጣኞችን ፎቶግራፎችን አጋርተዋቸዋል” ያለቻቸውን የአራት ፖሊሶች ስምም ጠቅሳ ነበር።
በአደጋው ኮቢና ልጁን ጨምሮ፣ ፓይለቱ፣ ሁለት የአስራ ሦስት ዓመት እድሜ ያላቸው የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች፣ ሦስት ወላጆችና አሰልጣኙ ህይወታቸው አልፏል።
በቅርጫት ኳሱም ሆነ በስፖርቱ ዓለም ስመ ገናና የነበረው ኮቢ ክለቡን ሎስ አንጀለስ ሌከርስን አምስት ጊዜ የሻምፒዮንነት ስፍራን ያስጨበጠና ሁለት ጊዜም የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያን ማሸነፍ ችሏል።
ኮቢ ከሃያ ዓመት የተሳካ የስፖርት ዓለም ቆይታው በኋላ ራሱን ከቡድኑ ያገለለው ህይወቱ ከማለፉ ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።












