ናይጄሪያ የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመግታት የጫካ ሥጋ ሽያጭን አገደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የናይጄሪያ መንግሥት የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥንቃቄ ለማገዝ የጫካ ሥጋ ሽያጭ ማገዱን ይፋ አደረገ።
ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ በናይጄሪያ ስድስት በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ባለሥልጣናቱ ገልፀው በዚህ ዓመት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 21 ደርሷል ሲሉ ይፋ አድርገዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቫይረሱ የተያዘ እንስሳ ሥጋን በመመገብ ከእንስሳ ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችል ባለሙያዎች ቢናገሩም ይህ በጣም የተለመደው የመተላለፊያ መንገድ አይደለም።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቀላል የቫይረስ ኢንፌክሽን ሲሆን በናይጄሪያ በስፋት ይታያል። በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች እና በሞቃታማ የዝናብ ደኖች አቅራቢያ ቫይረሱ የበለጠ ይስፋፋል።
እ.ኤ.አ. በ 2017 ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ናይጄሪያ አልፎ አልፎ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠቁ ሰዎች አጋጥመዋታል።
ቫይረሱ በዋነኛነት በደቡብ የአገሪቱ ክፍል የተገኘ ቢሆንም ከ2020 ጀምሮ ወደ መካከለኛ፣ ምሥራቅ እና ሰሜናዊ አካባቢዎች ተዛምቷል ሲልም የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
በዚህ ዓመት ከተረጋገጡት 21 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ሰው በበሽታ ህይወቱ ማለፉ ተዘግቧል።
ነገር ግን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የናይጄሪያ የጤና ኃላፊዎች “ምንም አዲስ ወይም ያልተለመደ የቫይረሱ ስርጭት የሚያሳይ ማስረጃ የለም፣ እንዲሁም በክሊኒካዊ መረጃዎቻችን ላይ የተመዘገበ ለውጥ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሳይንቲስቶች በአውሮፓ በቅርቡ እየጨመረ የመጣውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለማብራራት እየጣሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ይህ ወረርሽኝ ከአፍሪካ አገሮች ከሚደረግ ጉዞ ጋር እስካሁን አልተገናኘም። ነገር ግን ሳይታወቅ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ሲሰራጭ መቆየቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል።
አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ካለው ቫይረሱ ሊሰራጭ ይችላል። ቫይረሱ በተሰነጠቀ ቆዳ፣ በመተንፈሻ አካላት እና በዓይን ወደ ሰውነታችን ሊገባ ይችላል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠቁ ሰዎች የበሽታው ምልክት በሚያዩበት ወቅት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ተነግሯቸዋል።
በናይጄሪያ ለምግብነት የሚውሉ እንደ ቺምፓንዚዎች፣ የሌሊት ወፍ፣ አይጥ እና እባቦችን ጨምሮ ከጫካ አድኖ መመገብ የተለመደ ነው። ሥጋቸውም በከተሞች ይሸጣል።
ይህም በተለይም በገጠራማ የናይጄሪያ አካባቢዎች በጣም ወሳኝ የምግብ አማራጭ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ዘወትር ባይገኝም ተወዳጅ እና ውድ ምግብ ነው።
በዚህም ምክንያት በናይጄሪያ በርካታ የጫካ ሥጋ ገበያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ አሁን የተጣለው እገዳ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን እስካሁን ግልፅ አይደለም።
የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለሥልጣናት በእንስሳት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የዝንጀሮ በሽታ ለመለየት የሚያስችል ክትትል እንዲጨምሩም መመሪያ ሰጥቷል።
የመካነ እንስሳት፣ የፓርኮች እንዲሁም የልዩ ጥበቃ ቦታዎች እና የመዝናኛ ማዕከላት አስተዳደሮች በእንስሳትና በሰዎች መካከል ምንም አይነት ግንኙነት አለመኖሩን እንዲያረጋግጡም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።












