ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሪትኒ ስፒርስ የታዋቂው ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ጠባቂ ”በጥፊ መትቶኛል” ስትል ወቀሰች
ብሪትኒ ስፒርስ የወጣቱ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ቪክተር ዌምባናያማ ጠባቂ “በአይበሉባው በጥፊ ብሎኛል” ስትል ወቀሰች።
የላስ ቬጋር ፖሊስ አሪያ ሆቴል የተሰኘ አካባቢ አንድ ሰው ተመትቶ መጠራቱን ቢያምንም ማንም ሰው በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለ ገልጧል።
ብሪትኒ ስፒርስ በማሕበራዊ ሚድያ ገጿ የደረሰባት “እእምራዊ ጭንቀት ያስከተለ” ጉዳት ያልተጠበቀ እንደሆነ ፅፋለች።
ፈረንሳዊው ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ዌምቢ “ያየሁት ነገር የለም” ቢልም የሆነ ሰው እንደተገፋ አልካደም።
በቅርቡ ከወጣቶች ቁንጮ ሆኖ የተመረጠው የ19 ዓመቱ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ላስ ቬጋስ ውስጥ ምግብ ቤት እየጎበኘ ነበር።
“ቀረብ ብዬ እንኳ ደስ አለህ ልለው ነበር። በጣም ጫጫታ ስለነበር እንዲዞርልኝ ጀርባውን ነካ አደረግኩት” ብላለች ብሪትኒ።
ይሄኔ ነው የዌምባናያማ ጠባቂ ነው የተባለ ግለሰብ ብሪትኒ ስፒርስን በአይበሉባው በጥፊ እንደመታት የተነገረው።
ብሪትኒ እንደምትለው ጥፊው ያደረገችውን መነፅር እንዲወድቅና መሬት መንካት እስኪቀራት እንድትንገዳገድ አድርጓታል።
ዘፏኟ ወደማሕበራዊ ሚድያ ወጥታ የደረሰባትን እንድትናገር ያደረጋት የቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ አስተያየት እንደሆነ ገልጣለች።
ተጫዋቹ ለአንድ የሥፍራው ጋዜጣ “የሆነች ሴት ከጀርባ ስትጠራኝ ሰምቻለሁ። ከዚያም ግለሰቧ ከኋላ ጎተተችኝ” ኢሰል ተናግሯል።
“ጀርባየን ነካ ሳይሆን ያደረገችኝ፤ ወደኋላ ነው የጎተተችኝ።”
“ከዚያም ጠባቂዬ ገፋት። ምን ያህል ኃይል እንደተጠቀመ ባለውቅም እንደገፋት ግን አውቃለሁ። መቆም አልቻልኩም። ወደውስጥ ገብቼ እራቴን በልቼ ወጣሁ።”
ብሪትኒ ስፒርስ የላስ ቬጋስ ፖሊስ ላደረገላት ድጋፍ ምስጋና አቅርባለች።
የ41 ዓመቷ ብሪትኒ ስፒርስ ባለፈው ዓመት ከረዥም ጊዜ የፍቅር ጓደኛዋ ሳም አስጋሪ ጋር ትዳር መሥርታለች።
የ29 ዓመቱ አስጋሪ በማሕራዊ ሚድያ ገፁ ሚስቱን ደግፎ አስተያቱን ሰጥቷል።
“ይህ ግለሰብ ከጥፋቱ ተምሮ ለሴቶች ያለውን አመለካከት ይቀይራል የሚል ተስፋ አለኝ” ብሏል።
ብሪትኒ ስፒርስ በ2021 ለ13 ዓመታት ከቆየችበት የአባቷ አገዛዝ ተላቃለች።
አባቷ ጄሚ ስፒርስ በሕይወቷ በሁሉም መስኮች የበላይነት እንዲኖረው ሕጋዊ እውቅና ነበረው።
ከገንዘብ አጠቃቀም ጀምሮ፤ ትዳር መመሥረትና ልጆቿን መጎብኘት ትችል የነበረው ከአባቷ ፈቃድ ጠይቃ ነበር።