የስፔኗ ግዛት ሴቶች በመዋኛ ገንዳዎች ከወገብ በላይ እርቃናቸውን መሆን ይችላሉ አለች

የስፔን ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ካታሎኒያ ግዛት ሕዝብ በሚሰበሰብበት መዋኛ ገንዳዎች ሳይቀር ሴቶች ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን መሆን ይችላሉ አለች።

በ2020 በወጣው የእኩልነት ሕግ መሠረት ከወገብ በላይ ሆኖ በአደባባይ መታየት ፍቃድ ተችሮታል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የከተማ አስተዳደር መዋኛ ገንዳዎች ሴቶች ከወገብ በላይ እርቃናቸውን እንዳይታዩ መከልከላቸው ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።

አሁን ላይ የአካባቢ ባለስልጣናት የትኛውንም አይነት መድልዎ ማድረግ አትችሉም ተብለዋል።

ሴቶች ከወገብ በላይ እርቃናቸውን እንዳይሄዱ መከልከል “አድልዎ እና ሰዎች ሰውነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን ነጻ ምርጫ የሚጋፋ ነው” በማለት መቀመጫውን ባርሴሎና ያደረገው የካታላን መንግሥት ለታችኛው የመንግሥት አካላት በደብዳቤ አሳስቧል።

ግዛቷ ሴቶች ከፈቀዱ ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን እንዲታዩ ብቻ ሳይሆን የፈቀደችው፤ በሙስሊም ሴቶች የሚዘወተረው ሙሉ ሰውነት የሚሸፍ የመዋኛ ልብሰ መልበስ ይፈቃዳል ብላለች። በተጨማሪም ሴቶች በአደባባይ ጡት እንዳያጠቡ መከልከል የለባቸውም ብላለች የካታሎን ግዛት።

በሕጉ መሠረት የግዛቱ አስተዳዳሪዎችን ይህን መመሪያ የሚተላለፉ ከተማ አስተዳደሮችን እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዮሮ መቅጣት ይችላል።

በካታላን ሕጉ ተፈጻሚ አይደለም እያሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ከቆዩት መካከል ‘ሙግሮንስ ላሉረስ’ የተባለ የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን ቀዳሚው ነው።

የቡድኑ ቃል አቀባይ የሆነችው ማሪኦና ትራባል፤ “ይህ የጾታ እኩልነት ጉዳይ ነው።ወንዶች ከወገብ በላይ እርቃናቸውን እየሄዱ ሴቶች ግን አይችሉም” በማለት ተናግራለች።