በአሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት የእናቶች ሞት በእጥፍ መጨመሩን አንድ ጥናት ገለጠ

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በአሜሪካ የእናቶች ሞት በእጥፍ መጨሩን አንድ ጥናት ጠቆመ።

የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር ያወጣው ዘገባ እንደገለጠው በተለይ ደግሞ የጥቁር እናቶች ሞት ቁጥር እጅግ ከፍ ብሎ ታይቷል።

አሜሪካዊ ሕንዳዊ እና የአላስካ ቀደምት ነዋሪ እናቶች ከሌሎች በተለይ ከፍ ያለ ሞት አስመዝግበዋል።

በግዛት ሲከፈል ደግሞ በደቡባዊ አሜሪካ የሚገኙ ግዛቶች ከፍተኛ የእናቶች ሞት ተከስቶባቸዋል።

የእናቶች ሞት ማለት በእርግዝና ወቅት አሊያም ከወሊድ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ የሚከሰት ሞት ማለት ነው።

በፈረንጆቹ 1999 ከ100 ሺህ እናቶች 12.7 የሚሆኑት ይሞቱ ነበር። በ2019 ይህ ቁጥር ወደ 32.2 ከፍ ብሏል።

ጥናቱ ከኮሮናቫይረስ በኋላ ያለውን ጊዜ ያካተተ አይደለም።

ከሌሎች ጥናቶች በተለይ ይህ ጥናት በአሜሪካ ግዛቶች መካከል ያለውን ልዩነት የተመለከተ ሲሆን፣ አልፎም በአምስት ዘሮች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ልዩነትም አጥንቷል።

“የጤና ክትትል እና ለጤና ክትትል ዕድል አለማግኘት ምን ያክል ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ተረድተናል። ይህም መዋቅራዊ ዘረኝነት ምን ያክል እንዳለ ማሳያ ነው” ይላሉ ከአጥኝዎች መካከል አንዷ ዶ/ር አሊሰን ብራያንት።

ከ100 ሺህ አማካይ የእናቶች ሞት መካከል ጥቁር እናቶች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን፣ ባለፉት 20 ዓመታት በተለይ በሰሜን ምሥራቅ የአሜሪካ ግዛቶች ይህ ቁጥር ጨምሯል።

“ለወትሮው ደቡብ የሚገኙ ግዛቶች ነበሩ ከፍተኛ የእናቶች ሞት እንዳላቸው የሚነገረው። ነገር ግን ይህ ሁሉንም ነገር ግልጥ አድርጎ አያሳይም” ይላሉ ዶክተሯ።

የሚዙሪ ግዛት አገረ ገዢ የሆኑት ማይክ ፓርሰን በቅርቡ የእናቶች ሞትን ለማስወገድ ለወጣው ዕቅድ የሚሆን 4.4 ሚሊዮን ዶላር በጀት አፅድቀዋል።

በጥቁር እናቶች ዘንድ የሚታየው የሞት መጠን ከፍ ማለት ስለአሜሪካ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያው ውቅር ውይይት እንዲጫር ምክንያት ሆኗል።

የአሜሪካ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን የሆነችው ቶሪ ባዊ ባለፈው ግንቦት ከወሊድ ጋር በተያያዘ በ32 ዓመቷ መሞቷ ይታወሳል።

እናቶች ከወሊድ በኋላ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የአእምሮ ጤና መታወክ፣ ከልክ ያለፈ ደም መፍሰስ፣ የልብ ሕመም እና የደም ግፊት ጥቂቶቹ ናቸው።

ይህን የሚለው የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መካላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ነው።

ይፋ የሆነው ጥናት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል በቂ የሆነ ስለእናቶች ሞት የሚጠቁም መረጃ ማግኘት ነበር።

ዶክተር ብራያንት ከ2019 በኋላ ያለው ጊዜ ከግምት ውስጥ ቢገባ “በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የእናቶች ሞት መጨመር እናይ ነበር” ብለዋል።