መስክ የተረከበው ትዊተር የሠራተኞች ቅነሳ ሊያደርግ ነው

በቅርቡ ግዢው ተፈጽሞ ባለጸጋው ኤሎን መስክ የተረከበው ትዊተር፤ የሚሰናበቱ ሠራተኞቹን በተመለከተ ዛሬ ለተቀጣሪዎቹ ገለጻ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ግዙፉ የማሕበራዊ ትስስር ገጹ በውስጥ የኢሜል መስመሩ ለሠራተኞቹ በላከው መልዕክት ቅነሳው “ትዊተርን በጤናማ መንገድ ለማስቀመጥ” እየተደረገ ያለ ጥረት አካል ነው ብሏል።

ኩባንያው አክሎም ቢሮው በጊዜያዊነት የሚዘጋ ሲሆን የሠራተኞች የመግቢያ ካርድም ይታገዳል ብሏል።

ባለፈው ሳምንት በ44 ቢሊዮን ዶላር የትዊተርን ግዢ ያጠናቀቀው ቢሊየነሩ መስክ፤ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ይሆናል።

ከአርብ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ኃይላችንን ለመቀነስ በአስቸጋሪ ሂደት እናልፍለን ሲል ትዊተር ለሠራተኞቹ በላካው መልዕክት የገለጸ ሲሆን፤ “ውሳኔው ለትዊተር ዋጋ ያለው አስተዋጾ ያበረከቱ በርካታ ሰዎችን እንደሚነካ እንረዳለን። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ኩባንያውን በስኬት ለማስጓዝ ውሳኔው አስፈላጊ ነው” ሲል አክሏል።

በተጨማሪም ወደ ቢሮ የሚገቡ ሰዎችን በፍጥነት መገደብ አስፈልጓል ያለው ኩባንያው፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን "የእያንዳንዱን ሠራተኛ ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የትዊተርን ስርዓት እና የደንበኞችን መረጃ ለመጠበቅ“ ነው ብሏል።

ዛሬ ዓርብ ሁሉም ሠራተኞች “በትዊተር ያልዎት የስራ ድርሻ” በሚል ርዕስ መልዕክት የሚደርሳቸው ሲሆን ቅነሳው የማይመለከታቸው ሰዎች በኩባንያው ኢሜል መልዕክት ይደርሳቸዋል ተበሏል።

በሌላ በኩል በቅነሳው የሚካተቱ ሰዎች ቀጣዩ እርምጃ ምን እንደሆነ የሚገልጽ መልዕክት በግል የኢሜይል አድራሻቸው ይላክላቸዋል።

ይህ ከመሰማቱ ቀደም ብሎ መስክ ትዊተር ካለው አጠቃላይ ሠራተኛ ግማሽ ያህሉ ወይም 3 ሺህ 700 ሰዎችን የመቀነስ እቅድ እንዳለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ብሉምበርግ በስም ያልጠቀሳቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ፤ በኩባንያው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በስራቸው ካሉ ሠራተኞች መቀነስ አለባቸው የሚሏቸውን ሠራተኞች ስም ዝርዝር እንዲያቀርቡ ተጠይቋል።