የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የዓለም ጤና ስጋት ነው ተብሎ ታወጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ወረርሽኝ አንገብጋቢ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አወጀ።
በድርጅቱ ምደባ መሠረት ይህ ውሳኔ ከወረርሽኞች አሳሳቢነት አንጻር ከፍተኛው ደረጃ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በዓለም ዙሪያ እየጨመረ በመሄዱ ነው የሕዝብ ጤና ስጋት ተብሎ እንዲፈረጅ የተወሰነው።
ውሳኔው የተላላፈው የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት በቫይረሱ ዙሪያ ለሁለተኛ ጊዜ ማካሄድ በጀመረው የበሽታው የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ ስብሰባ ማብቂያ ላይ ነው።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ በ75 አገራት ውስጥ ከ16,000 በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል።
አስካሁን በበሽታው ምክንያት አምስት ሰዎች መሞታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የዓለም ሕዝብ የጤና ስጋት ተብለው የተለዩ ሁለት በሽታዎች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ለማጥፋት ትግል እየተደረገበት ያለው ፖሊዮ ናቸው።
በተካሄደው ስብሰባ ላይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽን ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ነው ተብሎ ይወሰን በሚለው ላይ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ የጋራ ስምምነት እንዳልነበረ ዶክትር ቴድሮስ ተናግረዋል።
ነገር ግን ወረርሽኙ በፍጥነት በዓለም ዙሪያ እየተዛመተ በመሆኑ፣ በእርግጥም ቫይረሱ የዓለም ሕዝብ ጤና ስጋት ነው የሚለውን ውሳኔ ማሳለፋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
“በዓለም ጤና ድርጅት ግምገማ የበሽታው ስጋት ከፍተኛ ስጋት ከሆነበት ከአውሮፓ በስተቀር በቀረው የዓለም ክፍል መካከለኛ ነው።”
በዓለም ዙሪያ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሽታው የበለጠ መስፋፋት ዕድሉ በአሁኑ ጊዜ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ወረርሽኙ በስፋት የበለጠ በዓለም ላይ የመስፋፋት ስጋት እንዳለ ግን ግልጽ ነው ሲሉ ባለሥልጣኑ አክለዋል።
ይህን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የዓለም የጤና ስጋት ነው ብሎ ድርጅቱ ማወጁ የመከላከያ ክትባት በፍጥነት እንዲዘጋጅና ቫይረሱ የበለጠ እንዳይዛመት ለማድረግ የሚያስፈልጉ የመከላከያ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲደረግ ያግዛል ብለዋል ዶክተር ቴድሮስ።
በተጨማሪም ድርጅቱ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ለመጠበቅና የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት አገራት እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርግ መመሪያን እያዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።
“ይህ ወረርሽኝ በትክክለኛ ዕቅዶችና በትክክለኛ ቡድኖች አማካይነት ለማስቆም የሚቻል ነው” ብለዋል ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በመጀመሪያ የተገኘው በማዕከላዊ አፍሪካ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ በ1950ዎቹ ነበር።












