አሜሪካ ሶማሊያ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ቁልፍ የአይሲስ መልማይን መግደሏን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት በፈጸመችው ጥቃት ቁልፍ የእስላማዊ መንግሥት (የአይሲስ) መልማይ ነው ያለችውን አህመድ ማኤሌኒኒኔን የተሰኘ ግለሰብ መግደሏን አስታወቀች።
አህመድ ከመልማይነት በተጨማሪ በአይሲስ የውጭ ኦፕሬሽን መሪነት ጂሃዲስቶችን በአሜሪካ እና በመላው አውሮፓ ያሰማራ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ይቆጣጠር እንደነበር የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) የካቲት 4/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ጥር 24/2017 ዓ.ም. በቅንጅት በፈጸሙት ጥቃት አህመድን ጨምሮ 14 የአይሲስ የሶማሊያ ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ዕዙ እስካሁን ባደረገው ግምገማ ንጹሃን ሰዎች አለመጎዳታቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የተቀናጀው የአየር ጥቃት ኢላማ ያደረገው የአይሲስ የሶማሊያ ከፍተኛ አመራሮች መሆኑን አመላክቷል።
የአየር ጥቃቶቹ የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር የፑንትላንድ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ቦሳሶ በስተደቡብ ምሥራቅ 80 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኙ ዋሻዎች ላይ መፈጸማቸው ተገልጿል።
"አሜሪካ እና ሌሎች አጋሮችን በጥቃቶቻቸው ስጋት ላይ የጣሉ አይሲስ እና ሌሎች የአሸባሪ ድርጅቶችን ማሽመድመድ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ ተልዕኮ ዋነኛ ሥራ ነው" ብሏል አፍሪኮም በመግለጫው።
ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ፑንትላንድ ውስጥ ከፍተኛ የአይኤስ ጥቃቶችን አቀነባባሪ እና ሌሎች ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት "[ታጣቂዎች] የሚኖሩባቸውን ዋሻዎች ማውደሙን እና በምንም መልኩ በንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ብዙ አሸባሪዎችን መግደሉን" ተናግረዋል።
"ባይደን እና ጓደኞቹ ሥራውን ለመጨረስ በፍጥነት እርምጃ አልወሰዱም። እኔ ግን ያንን አደረግኩ" ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያልቻሉትን እሳቸው ማሳካታቸውን በኩራት ገልጸዋል።
የፑንትላንድ የፀረ-ሽብርተኝነት አካሄድ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ግንኙነቷን ካቋረጠችው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ከወሰደው የተለየ ነው።
አሜሪካንን እና ቱርክን የመሳሰሉትን ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች በሚሰጥ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ያልሆነ እና በራሱ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 12,000 የሚጠጉት እዚያው ሶማሊያ ውስጥ ይገኛል።
የፑንትላንድ የፀጥታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሙባረክ እንዳመለከቱት ከሰሜን-ምሥራቅ የተወጣጡ ወታደሮች ከአይኤስ ጋር ሲዋጉ የቆዩት ከጥቂት እርዳታ እና ድጋፍ ጋር ነው።

የፎቶው ባለመብት, HCAP
የአይኤስ-ሶማሊያ ምልምል ዋና ምንጭ በፑንትላንድ የወደብ ከተማ ቦሳሶ በኩል ባሕር አቋርጠው ወደ ውጭ አገር ለመሻገር ተስፋ የሰነቁ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
አይኤስ ለስደተኞቹ በባሕረ ሰላጤው ሀገራት ከሚያገኙት የተሻለ ክፍያ የሚያቀርብላቸው ሲሆን፣ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዦች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
"አይኤስ-ሶማሊያ ውስጥ 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የውጭ ተዋጊዎች መሆናቸውን ገምግመናል፣ በአብዛኛው ከሰሜን አፍሪካ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከታንዛኒያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ተዋጊዎች ናቸው" ብለዋል የፑንትላንድ የፀጥታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሙባረክ።
ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ ኃላፊ ማይክል ላንግሌይ አይኤስ በሰሜናዊ ሶማሊያ በአንድ ዓመት ውስጥ "በሁለት እጥፍ" ያደገ መስሏቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ቡድኑ በታኅሣሥ ወር ፑንትላንድ ባሪ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የጦር ሰፈር በመምታት ካካሄዳቸው እጅግ የተራቀቁ ጥቃቶች መካከል አንዱን ፈጽሟል።
ቡድኑ አንድም ሶማሌያዊ በጥቃቱ አልተሳተፈም ሲል መግለጫ አውጥቷል። 12ቱ አጥቂዎች ከሰባት ሀገራት ማለትም ከታንዛኒያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሮኮ፣ ከሊቢያ፣ ከቱኒዚያ፣ ከየመን እና ከኢትዮጵያ የመጡ ናቸው።
እንቅስቃሴው ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድም የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።
የአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሶማሊያ ባለሙያዎች የአይኤስ የፋይናንስ መሠረት ቁልፍ አካል የሆነው የአል-ካራር ጽህፈት ቤት በፑንትላንድ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ እና ከዚያም ባሻገር ላሉ የቡድኑ ቅርንጫፎች የገንዘብ እና እውቀት ድጋፍ ይሰጣል።












