በናይጄሪያ 10 ሰዎች ተገድለው ከ160 የማያንሱ ሰዎች ታግተው ተወሰዱ

በናይጄሪያ ማዕከላዊ ኒጀር ግዛት 10 ሰዎች መሞታቸውን እና ቢያንስ 160 የሚሆኑ የመንደሩ ነዋሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን ባለስልጣናት ገለጹ።

ከናይጄሪያው አክራሪ እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሃራም እንደሆኑ የተጠረጠሩ በርካታ ታጠቂ ኃይሎች አርብ ምሽት ኩቺ የምትባል መንደርን መውረራቸውን የአካባቢው ባለስልጣን አሚኑ አብዱልሀሚድ ናጁሜ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታግተው የተወሰዱት አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት ሲሆኑ የተገደሉት ደግሞ ለአካባቢው ጥበቃ የሚያደርጉ አዳኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ በሞተር ሳይክሎች ወደ ኩቺ የገቡ ሲሆን ምግብ እያበሰሉ እና እየተመገቡ፤ ሻይ እያፈሉ እንዲሁም ቤቶችን እየዘረፉ ከሁለት ሰዓታት በላይ ቆይተዋል።

የኩርቺ ማህበረሰብ አባላት እገታውን ተከትሎ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የሙንያ አስተዳደር ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ናጁሜ ተናግረዋል።

በጅምላ አፈናው ጥልቅ ስጋት እንደገባው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በማህበራዊ ድረ-ገጾቹ ላይ አስፍሯል።

"መንደሩ በታጣቂዎች መወረር የናይጄሪያ ባለስልጣናት ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ስላለመጠበቁ ሌላው ማሳያ ነው" ብሏል።

አምነስቲ ከእአአ ከ2021 ጀምሮ ታጣቂዎች የኩቺ መንደርን በተከታታይ እያጠቁ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በቤታቸው እየደፈሩ ነው ያለ ሲሆን፤ "ከጊዜ ወደ ጊዜ ታጣቂዎቹ ከእገታ መዳን የሚፈልጉ ሰዎችን በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየጠየቁ ነው" ሲል በመግለጫው አትቷል።

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ፤ "የናይጄሪያ ባለስልጣናት እነዚህን ተደጋጋሚ አፈናዎች እንዲያቆስም እና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይጠይቃል። ተደጋጋሚ የጅምላ አፈና እና ግድያ ባለስልጣናት ህዝቡን ከጥቃት በመከላከል ረገድ እንዳልተሳካላቸው ግልጽ ማስረጃ ነው" ብሏል።

በኒጀር ግዛት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መጥተዋል። አንዳንድ ጊዜም ታጣቂዎቹ ከጂሃዲስት ቡድኖች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ግልጽ አይደለም።

ከእገታ ለሚገኝ ገንዘብ ሲባል ባለፈው ወር በርካታ መንደሮች በታጠቂዎች ዒላማ ሆነዋል።