ህወሓት በትግራይ ኃይል አባላት ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

የትግራይ ኃይሎች አባላት በሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Woyen

የምስሉ መግለጫ, ህወሓት የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው በትግራይ ኃይሎች ካምፕ ላይ ነው ይላል

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን ጥቃት በመፈጸም በትግራይ ኃይሎች አባላት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገለጸ።

ህወሓት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ከአፋር ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ አርብ ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም. ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ዝርዝሩን ባይገልጽም ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።

ይህ የድሮን ጥቃት በአካባቢው በነበሩ የትግራይ ሠራዊት አባላት እና ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል ያለው መግለጫው፣ ይህ የድሮን ድብደባ ፕሪቶሪያ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ የጣሰ እና የከፋ አደጋ ውስጥ የከተተ ነው ብሏል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የህወሓት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ የተፈጸመው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው።

ባለሥልጣኑ ጥቃቱ የተፈፀመው በትግራይ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሚገኝ ሚልካ በሚባል ወታደራዊ ካምፕ ላይ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ህወሓት በመግለጫው በኃይሎቹ ላይ ጉዳት መድረሱን ብቻ የጠቀሰ ሲሆን፣ ወታደራዊ ባለሥልጣኑ ግን "አነስተኛ" ያሉት ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት በስልክ እና በጽሁፍ መልዕክት አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

ህወሓት ባወጣው መግለጫ "በትግራይ ሕዝብ ሞት እና ስቃይ የሚረካው የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ወደ መጣስ ተሸጋግሯል'' በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይመጣ የበኩሉን ይወጣ ሲል ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የድሮን ጥቃት በትግራይ ኃይሎች ካምፕ ላይ መድረሱ የተሰማው የአፋር ክልል የትግራይ ክልል ኃይሎች ወደ 15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ ከከሰሰ በኋላ ነው።

የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ "የከፈትነው ጥቃትም ሆነ የተቆጣጠርነው መሬት የለም" ሲል ውንጀላውን አስተባብሏል።

የአፋር ክልል በበኩሉ በጥቃቱ በአካባቢው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል።

ከሕጋዊ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት አርብ ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያን ስምምነት በመጣስ ጥቅምት 28 ማለዳ የድሮን ጥቃት ፈጽሟል ሲል ከስሷል።

የአፋር ክልል መንግሥት "የህወሓት ቡድን" ሲል የጠራውን ኃይል በክልሉ ዞን ሁለት መጋሌ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "የከባድ መሳሪያ ተኩስ መክፈቱን" በመግለጽ የከሰሰው ረቡዕ ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነበር።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ሐሙስ ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የትግራይ ክልል ኃይሎች "ወደ አፋር ክልል ዘልቀው ጥቃት ፈጽመዋል" መባሉን አስተባብሏል።

የአፋር ክልል ይህንኑ በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ መሠረተ ቢስ ሲል ያጣጣለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በትግራይ በኩል የሚፈጠር "ሁከትም" ይሁን "አለመረጋጋት" እንዲኖር "በፍጹም እንደማይፈልግ" ጨምሮ ገልጿል።

የመጋሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አብዱ ሼክ በራህ ኡስማን ለቢቢሲ የትግራይ ኃይሎች "በሞርታር እና በዙ-23" ከባድ መሳሪያዎች ተኩስ መከፈታቸውን የአካባቢው ነዋሪም "ተደናግጦ፣ መሸሹን" ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው ከአካባቢው የሸሸው ማኅበረሰብ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልተናገሩም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት አንዳቸው ሌላኛቸውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን በመጣስ ይከስሳሉ።

ሰኞ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም. ከአምስት ዓመት በፊት በትግራይ ውስጥ በነበረው የአገሪቱ ጦር ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር ለተሰበሰቡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የአገሪቱ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ባደረጉት ንግግር ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥሱ ተደጋጋሚ ተግባራት ፈጽሟል ሲሉ ከስሰው ነበር።

"ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሠራቸው ትንኮሳዎች፣ ሥራዎች እና ሴራዎች ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ናቸው፤ ከበቂም በላይ ነበሩ" በማለት ምክንያቶቻቸውን ዘርዝረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሐሙስ ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የፌደራል መንግሥቱ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት "በአግባቡ እንዲፈጸም አላስቻለም" ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ነበር።

ባለፉት ወራት በፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እና በህወሓት መሪዎች መካከል የሚካሄደው መካሰስ ዳግም ግጭት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።