የቅንጡ ምርቶች ነጋዴው ቁጥር አንድ አፍሪካዊ ባለሃብት ሆኑ

ጆሃን ሩፐርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጆሃን ሩፐርት

ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊዬነር ጆሃን ሩፐርት ናይጄሪያዊውን አሊኮ ዳንጎቴን በመብለጥ የአህጉራችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ሰው ሆኑ።

ሩፐርት የሚያስተዳድሩት ሮችመንት የተሰኘው ኩባንያ በስሩ ያሉ ድርጅቶች ጌጣ ጌጦችን፣ የእጅ ሰዓት፣ የቆዳ ምርቶች፣ ልብስ እና ጦር መሳሪያዎችን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ።

እንደ ብሉምበርግ የቢሊየነሮች ዝርዝር ከሆነ ደቡብ አፍሪካዊው የተጣራ ንብረታቸው ከ1.9 ወደ 14.3 ቢሊዮን በፍጥነት በመጨመር ቁጥር አንድ አፍሪካዊ ባለጸጋ አድርጓቸዋል።

በአንጻሩ የአሊኮ ዳንጎቴ ንብረት በዚህ ዓመት ብቻ በ1.7 ቢሊዮን ዶላር ቀንሶ የተጣራ ሃብታቸው 13.4 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል።

ለዳንጎቴ የተጣራ ሃብት መቀነስ ምክንያቱ አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ በሚያደርጉባት የትውልድ አገራቸው ያለው ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ ነው ተብሏል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ነዳጅ ላይ ይደረግ የነበረ የ30 በመቶ ድጎማ ማንሳትን የሚጨመር በአገሪቱ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው በናይጄሪያ የዋጋ ንረት ተከስቷል።

ይህ ተከትሎ የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ናይራ ከአሜሪካ ጋር ያለው ተመን በመቀነሱ የዳንጎቴ የተጣራ ሃብት እንዲቀንስ አድርጓል።

የ66 ዓመቱ ዳንጎቴ ባለጸጋ የሆኑት በሲሚንቶ እና ስኳር ኢንዱስትሪዎቻቸው ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ በናይጄሪያዋ ትልቋ ከተማ ሌጎስ የነዳጅ ማጣሪያ ከፍተዋል።

ዳንጎቴ ከ9 ወራት በፊት በፎርብስ ጋዜጣ ለተከታታይ 13 ዓመታት ቁጥር አንድ የአፍሪካ ባለሃብት ተብለው ነበር።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በብሉምበርግ መሠረት ደረጃቸው ወደ ሁለት ዝቅ ብሎ በዓለም ደግሞ 159ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የሩፐርት ገቢ ደግሞ በከፍተኛ መጠን የጨመረው የቅንጡ ምርቶች ፈላጊ በመጨመሩ ነው።

መቀመጫውን ስዊትዘርላንድ ካደረገው ሪችሞንት በተጨማሪ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ባደረገው ሬምጋሮ በተሰኘው የፋይናንስ አግልገሎት በሚሰጠው ኩባንያቸው ስር በማዕድን እና ነዳጅ ማውጣት፣ በታሸጉ መጠጦች እና ምግቦች ዘረፍ ተሰማርተዋል።

የሩፐርት ሃብት ምንጭ ከአባታቸው የወረሱት ቢሆንም ባለፉት በርካታ ዓመታት የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በማስፋት ስኬታማ የሆኑ ኩባንያዎችን ማቋቋም ችለዋል።

መኖሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታወን ያደረጉት ቢሊየነሩ በለንደን እና ጄኔቫ ግዙፍ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች አሏቸው።

ከሩፐርት እና ዳንጎቴ በመቀጠል ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ኒኪ ኦፕንሃይመር በሦስተኛ ድረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ይህ ደቡብ አፍሪካዊ 11.3 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው።

ከእርሳቸው በመቀጠል ግብጻዊው ነጋዴ ናሴፍ ሳዊሪስ በ9.48 ቢሊዮን ዶላር ሃብት አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ናሪ ኪርሽ በ9.22 ቢሊዮን ዶላር አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ባለሃብት ናቸው።