ሊባኖስ ውስጥ ከፈነዱት የመልዕክት ማስተላለፊያዎች ጀርባ ያለው የታይዋን ኩባንያ

ማክሰኞ እና ረቡዕ ሊባኖስን ያናወጧት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍንዳታዎች በአስር የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድሉ ሺዎች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህም ሳቢያ አገሪቱ በከባድ ሐዘን፣ ድንጋጤ እና ፍርሃት ውስጥ ትገኛለች።

እነዚህ በተመሳሳይ ጊዜ ከዋና ከተማዋ ቤይሩት እስከ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙት ፍንዳታዎች በዓለም ላይ ከዚህ ቀደም ከታዩት ለየት ያሉ ናቸው። ምክንያቱም በተለያዩ ሰዎች እጅ ላይ የነበሩ የመገናኛ መሳሪያዎች ተከታትለው መፈንዳታቸው ነው።

ምንም እንኳን እስራኤል ስለፍንዳታዎቹ መረጃ ከመስጠት በትቆጠብም የሄዝቦላህ መሪዎች እና የደኅንነት ምንጮች የዚህ መጠነ ሰፊ ፍንዳታ አቀናባሪ የእስራኤል የስላላ ተቋም፣ ሞሳድ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።

ፍንዳታዎቹን ተከትሎ እንዴት በሺዎች የሚቆጠሩት ትናንሽ የመልዕክት መለዋወጫ መሳሪያዎች ላይ የሚፈነዱ ቁሶች ሊጠመዱባቸው ቻለ? የሚለው ከአደጋው በኋላ የተነሳ ጥያቄ ነው።

የመሳሪያዎቹ አምራች ደግሞ ከእስራኤልም ሆነ ከመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ጋር ግልጽ ግንኙነት ከሌለው ስፍራ መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ እንግዳ አድርጎታል።

የሳምንቱ ዋኛ ጉዳይ የሆነው ፍንዳታን በተመለከተ ፈጻሚው የእስራኤል የስላላ ድርጅት መሆኑ በስፋት ቢነገርም፤ የመሳሪያዎቹ አምራች ደግሞ ስሙ ለብዙዎች እንግዳ የሆነው የታይዋን ኩባንያ መሆኑ ክስተቱ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ደቡብ እስያ ድረስ ያነካካ ሆኗል።

ነገር ግን በድንገት የዓለም አቀፍ ትኩረት በመሆን ቀወስ ውስጥ የገባው የታይዋኑ ተቋም ‘ጎልድ አፖሎ’ መሥራች ቺንግ-ኩዋንግ ኩባንያቸው ከሊባኖሱ ጥቃት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት እንደሌለው አስተባብለዋል።

ከዚያ ይልቅ ኩባንያው የግንኙነት መሳሪያዎቹን ለማምረት የንግድ ምልክቱን እና ስሙን እንዲጠቀም ሃንጋሪ ውስጥ ለሚገኘው ‘ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ’ ለተባለ ኩባንያ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል። ቢቢሲ የተባለውን ድርጅት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የካምፓኒው መሥራች ጨምረውም “ከሊባኖስ የሚወጡ ምሥሎችን ከተመለከታችሁ፤ በፈነዱት ፔጀሮች ላይ በታይዋን የተሠራ የሚል ጽሁፍ የለባቸውም፤ እኛም አልሠራናቸውም” ሲሉ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ታይዋን ዋና ከተማ ታያፒ ውስጥ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ተከትሎ እስከነበረው ዕለት ድረስ የ‘ጎልድ አፖሎ’ ዌብሳይት ላይ ትንንሾቹ የመገናኛ መሳሪያዎች (ፔጀር) ምንነት እና እንዴት እንደሚሠሩ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃን ማንም ሰው በቀላሉ ማግኘት ይችል ነበር። ነገር ግን ሊባኖስ ውስጥ ለተፈጸመው ጥቃት መሳሪያ የሆኑት ምርቶች ከዚህ ድርጅት የወጡ ናቸው መባሉን ተከትሎ ዌብሳይቱ ከዕይታ ውጪ ሆኗል።

የኩባንያው መሥራች እንደሚሉት በሊባኖሱ ጥቃት ጥቅም ላይ የዋሉት ፔጀሮች በትክክልም በሃንጋሪያው ድርጅት የተመረቱ መሆናቸውን እና ድርጅቱም ከሦስት ዓመት በፊት ከጎልድ አፖሎ ጋር የማምረት ፈቃድ ስምምነት ማድረጉን አመልክተዋል።

ጨምረውም ሁለቱ ኩባንያዎች ለደረሱት ስምምነት ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ ገንዘብ የሚከፍልበት መንገድ “እምብዛም ያልተለመደ” መሆኑን እና በክፍያ በኩል ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር አመልክተዋል። ክፍያው ሲፈጸም የነበረው በመካከለኛው ምሥራቅ በኩል መሆኑን በመጥቀስ ቺንግ-ኩዋንግ ለጋዜጠኞች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የሃንጋሪው ኩባንያ ወደ ታይዋኑ ተቋም መጀመሪያ የቀረበው የጎልድ አፖሎ ፔጀሮችን በመግዛት አውሮፓ ውስጥ ለመሸጥ ሃሳብ ይዞ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ከአምራቹ ፈቃድ በመውሰድ ፔጀሮቹን በራሱ ፈብርኮ ለመሸጥ አዲስ ዕቅድ ይዞ ቀረበ።

በዚህ በኩልም ጎልድ አፖሎ “የምርቱን የንግድ ምልክት ፈቃድ ከመስጠት ውጪ በዲዛይንም ሆነ በማምረት ሂደት ውስጥ ተሳትፎ የለንም” ሲል ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

ነገር ግን የታይዋን ባለሥልጣናት በዚህ በኩባንያው ምላሽ ሙሉ ለሙሉ ባለመተማመናቸው በተቋሙ ውስጥ የምርመራ ቡድን አሰማርተው ማጣራት እያካሄዱ ነው።

በተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶች የምትታወቀው ታይዋን በርካታ ትናንሽ ኩባንያዎች የሚሳተፉባቸው ውስብስብ ሂደት ያሏት ሲሆን፣ እብዛኞቹ የሚሸጧቸውን ምርቶች እራሳቸው አይሰሯቸውም።

ኩባንያዎቹ የንግድ ምልክት እና የፈጠራ መብት ባለቤት ሊሆኑ እና የዲዛይን እንዲሁም የምርምር ክፍሎች ሊኗሯቸው ይችላል። ነገር ግን አብዛኛው የማምረት ሥራ የሚከናወነው በቻይና ወይም በሌሎች የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ውስጥ ነው።

የመልዕክት ማስተላላፊያ የሆኑት ፔጀሮች ደግሞ እጅግ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎች ባለመሆናቸው በመላው ዓለም ባሉ በርካታ ኩባንያዎች ይመረታሉ።

ባለስክሪኖቹ በመጠናቸው ትንሽ የሆኑት ፔጀሮች በራዲዮ ሞገድ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ለመላክ እና ለመቀበል ጥቅም ላይ ይውላሉ። በአውሮፓውያኑ 1980ዎች እና 1990ዎች በስፋት የተዋወቁት ኤሌክትሮኒክ ፔጀሮች ከሞባይል ስልኮች በፊት ተቋማት ለሠራተኞቻቸው አጭር መልዕክት ለመላክ ይጠቀሙባቸው የነበረ ሲሆን በአስር ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች እጅ ውስጥ ነበሩ።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ግን ዘመናዊ ሞባይል ስልኮች በመስፋፋታቸው ፔጀሮችን ከመጥፋት አፋፍ ላይ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል። ሌሎች የግንኙነት መስመሮች ቢቋረጡ እንኳን አስተማማኝ እና በዋጋ ርካሽ የሆኑት ፔጀሮች በአሁኑ ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት በሆስፒታሎች ውስጥ ለዶክተሮች እና ለነርሶች መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2000 ማብቂያ ገደማ አካባቢ አንስቶም የታይዋኑ ጎልድ አፖሎ እነዚህን ኤሌክትሮኒክ ፔጀሮች ምርቱን በመቀነስ በዋናነት ምግብ ቤቶች ተገልጋዮችን ለማስተናገድ ወደሚያግዘው የአጭር ርቀት የሬዲዮ መልዕክት ማስተላላፊያ ወደ መሥራት ፊቱን አዙሯል።

አስተማማኝ የሚባለውን ፔጀር የሚያመርተው የጎልድ አፖሎ ስምን በመጠቀም በሄዝቦላህ እጅ የገቡትን ምርቶች ለመሸጥ አንድ አካል ተጠቅሞበት ሊሆን እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

ነገር ግን አሁን ሊባኖስ ውስጥ ፈንድተው የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉት እና ሺዎችን ያቆሰሉትን የመገናኛ መሳሪያዎችን በተመለከተ አሁንም በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

የጎልድ አፖሎ ፔጀሮቹን የማምረት መብት ገዝቷል የተባለው የሃንጋሪው ቢኤሲ ኮንሰልቲን ካምፓኒን በተመለከተ እስካሁን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። በተጨማሪም ከዚህ ተቋም ጀርባ ያለው ማን ነው? የሚለው ብዙዎች በእርግጠኝነት ለማወቅ የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

ጥቃት ለማድረስ ለፍንዳታ ጥቅም ላይ የዋሉትን ፔጀሮች ጎልድ አፖሎ ካላመረታቸው አምራቹ ማን ነው? የትስ ተመረቱ? እንዴትስ ሄዝቦላህ እጅ ሊገቡ ቻሉ? የሚሉት ገና ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ሆነዋል።