ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤል የስለላ ተቋም በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙ ናቸው የተባሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍንዳታዎች
ሄዝቦላህ ለመረጃ ልውውጥ ሚጠቀምባቸው ‘ፔጀሮች’ ማክሰኞ ዕለት በተመሳሳይ ሰዓት መፈንዳታቸውን ተከትሎ ሊባኖስ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።
ቢያንስ 9 ሰዎች ተገድለዋል። 2 ሺህ 800 ያህሉ ሲቆስሉ አብዛኛዎቹ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።
ምንም እንኳን ሄዝቦላህ ባላንጣውን እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርግም ይህ ውስብስብ ጥቃት እንዴት እንደደረሰ ግልጽ አይደለም። የእስራኤል ባለሥልጣናትም እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በዚህ ፍንዳታ ዙሪያ እስካሁን የሚታወቁ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አጠናቅረናል።
ፍንዳታዎቹ መቼ እና የት ተከሰቱ?
ፔጀር አነስተኛ ገመድ አልባ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሲሆን፣ የድምጽ እና የጽሑፍ መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ያግዛል። ተንቀሳቃሽ ስልኮች ክትትል ስር ሊገቡ ስለሚችሉ እና የመጠለፍ ስጋት ስላለባቸው አንዳንዶች ፔጀርን ተመራጭ ያደርጉታል።
ማክሰኞ ዕለት መስከረም 7/2017 ዓ.ም. በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከቀኑ 9፡45 ሰዓት ገደማ ፍንዳታዎች አጋጠሙ።
የርችት እና የጥይት ድምጽ የሚመስሉ ትናንሽ ፍንዳታዎችን ከመስማታቸው በፊት ከሰዎች ኪስ ውስጥ ጭስ ሲወጣ ማየታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
በአንድ የደኅንነት ካሜራ ላይ በግብይት ላይ ከነበረ አንድ ግለሰብ ኪስ ውስጥ ፍንዳታ መፈጠሩ ታይቷል።
ከመጀመሪያዎቹ ፍንዳታዎች በኋላ ሌሎቹ ፍንዳታዎች ለአንድ ሰዓት ያህል ቀጥለዋል ሲል የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በመላው ሊባኖስ ወደ ሚገኙ ሆስፒታሎች ማቅናት መጀመራቸውን እና ይህም ግራ መጋባት መፍጠሩን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።
‘ፔጀሮች’ እንዴት ሊፈነዱ ቻሉ?
በማክሰኞው የጥቃት መጠን መደናገጣቸውን ተንታኞች በፍጥነት ገልጸዋል። ሄዝቦላህ በፀጥታ ጥበቃው የሚኮራ ነበር።
አንዳንዶች ጠለፋ ተፈጽሞ የፔጀሮቹ ባትሪዎች ከመጠን በላይ እንዲሞቁ በማድረግ መሳሪያዎቹ እንዲፈነዱ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም።
በርካታ ባለሙያዎች ግን ይህ የማይቻል ነው ይላሉ። ምክንያት የሚሉት ደግሞ ፍንዳታዎቹ ከባትሪዎቹ ከፍተኛ ሙቀት ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው ነው።
አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ከአቅርቦት ሰንሰለት ጋር የተያያዘ ጥቃት ሊሆን ይችላል። በዚህም ፔጀሮቹ በምርት ወይም በሽያጭ በሚተላለፉበት ወቅት እንዲፈነዱ ሆነው ተዘጋጅተዋል የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።
በሳይበር ሴኪዩሪቲ ዘርፍ የምርት እና የግብይት ሰንሰለት ጥቃቶች እያደጉ ከመምጣታቸው ባለፈ አሳሳቢ ሆነዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠላፊዎች በምርት ሂደት ላይ ቁሶችን ማግኘት በመቻላቸው በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ግን በመደበኛነት ከሶፍትዌር ጋር የተያያዙ ናቸው። የአቅርቦት ሰንሰለትን ሰርጎ መግባትን ስለሚጠይቅ ቁሱን ተጠቅመው የሚደርሱ ጥቃቶች በጣም ጥቂት ናቸው።
ይህ በእርግጥም የአቅርቦት ሰንሰለት ጥቃት ከሆነ ፔጀሮቹን ለማግኘት በምሥጢር የሚከናወን ትልቅ ሥራ መከናወኑን ያሳያል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቀድሞ የእንግሊዝ ሠራዊት ባለሙያ መሳሪያዎቹ ከ10 እስከ 20 ግራም የሚደርሱ ከፍተኛ ወታደራዊ ደረጃ ያላቸው ፈንጂዎች በሐሰተኛ የኤሌክትሮኒክስ አካል ውስጥ ተተክለው ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስለ ተጎጂዎች ምን ይታወቃል?
ለሄዝቦላህ ቅርብ የሆነ ምንጭ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸው ከተገደሉት መካከል ሁለቱ የሁለት የሄዝቦላህ የፓርላማ አባላት ልጆች ናቸው። የሂዝቦላህ አባል የሆኑ ግለሰብ ሴት ልጅ መገደሏንም ተናግረዋል።
ከቆሰሉት መካከል ደግሞ በሊባኖስ የኢራን አምባሳደር ሞጅታባ አማኒ ይገኙበታል። የኢራን መገናኛ ብዙኃን ጉዳቱ ቀላል ነው ብለዋል።
የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ በፍንዳታዎቹ አልተጎዱም ሲል ሮይተርስ ምንጩን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሊባኖስ የሕብረተሰብ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፍራስ አቢያድ አብዛኛው ጉዳት በእጅ እና በፊት ላይ የደረሰ ነው ብለዋል።
“አብዛኞቹ ጉዳቶች በፊት ላይ እና በተለይም በዓይን እንዲሁም በእጆች ላይ ደረሱ ሲሆን፣ የተወሰኑትም ጣቶቻቸው ተቆርጠዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ አወር ተናግረዋል።
“ወደ ድንገተኛ ክፍል የሚመጡት አብዛኞቹ ሰዎች የሲቪል ልብስ በመልበሳቸው የሄዝቦላህ ወይም ሌሎች ቡድኖች አባል መሆናቸውን ለመለየት በጣም ከባድ ነው…” ሲሉም አክለዋል።
“አዛውንቶች ወይም በጣም ወጣት የሆኑ ሰዎችንም እያየን ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ እንደሞተው ሕፃን… እና አንዳንዶቹም የጤና ባለሙያዎች ናቸው።”
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ ቡድን በበኩሉ ከሊባኖስ ውጭ በጎረቤት ሶሪያ በደረሰ ተመሳሳይ ፍንዳታ 14 ሰዎች ቆስለዋል።
ተጠያቂው ማነው?
እስካሁን ለጥቃቱ ማንም ኃላፊነቱን የወሰደ የለም። የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሄዝቦላህ ግን እስራኤል ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ እንዳሉት ፍንዳታዎቹ “የሊባኖስን ሉዓላዊነት የጣሱ እና በሁሉም ደረጃ ወንጀል” ሲሉ ይከሳሉ።
ሂዝቦላህ ከጥቃቶቹ ጀርባ እስራኤል ትገኛለች በሚል በሰጠው መግለጫው አገሪቱ “ሲቪሎች ላይ ላነጣጠረ የወንጀል ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ናት” ብሏል።
“ይህ ተንኮለኛ እና ወንጀለኛ ጠላት ቅጣቱን ይቀበላል” ሲል ዝቷል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት አስተያየት ባይሰጡም አብዛኞቹ ተንታኞች ከጥቃቱ ጀርባ መኖሯ እንደማይቀር ይስማማሉ።
በላንካስተር ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ሲሞን ማቦን “እስራኤል ኢላማዋን ለመከታተል ቴክኖሎጂን የመጠቀም ታሪክ እንዳላት እናውቃለን” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የቻተም ሐውስ ባልደረባ ሆኑት ሊና ካቲብ በበኩላቸው እስራኤል በሂዝቦላህ “የግንኙነት መረብ” ውስጥ “በጥልቀት ዘልቃ” መግባቷን የሚጠቁም ጥቃት ነው ብለዋል።
ሄዝቦላህ ለምን ፔጀር ይጠቀማል?
የእስራኤልን ክትትል እና ስለላን ለማምለጥ በሚል ሄዝቦላህ ዝቅተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀመውን ፔጀርን በስፋት ይጠቀማል።
ፔጀር የገመድ አልባ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያ ሲሆን፣ የጽሑፍ ወይም የድምጽ መልዕክቶችን ተቀብሎ የሚያስተላልፈ መሣሪያ ነው።
ተንቀሳቃሽ ስልክ በቀላሉ ለአደጋ ያጋልጣል በሚል ሄዝቦላህ መጠቀም ካቆመ ቆይቷል። የሐማሱ ቦምብ ሠሪ የሆነውን ያህያ አያሽን ለመግደል እስራኤል ተንቀሳቀሽን ስልኩን ያፈነዳቸው እአአ በ1996 ነበር።
በዚህም ሳቢያ ሄዝቦላህ ሞባይል ስልክ መጠቀም በእራኤል ኢላማ ውስጥ በማስገባት ለአደጋ አጋላጭ መሆኑን ከተገነዘበ መሰናባበቱን ያሳያል።
አንድ የሄዝቦላህ ባልደረባ ለኤሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደገለጹት፣ ፔጀሮቹ አዲስ እና ቡድኑ ከዚህ በፊት ያልተጠቀመባቸው ናቸው።
የሲአይኤ የቀድሞ ተንታኝ ኤሚሊ ሃርዲንግ በበኩላቸው “የደኅነት ጥሰቱ ለሄዝቦላህ እጅግ አሳፋሪ የሚባል ነው” ብለዋል።
“የጥቃቱ መጠን አካላዊ ጉዳት ብቻ የሚያስከትል ሳይሆን አጠቃላይ የፀጥታ መዋቅራቸውን እንዲጠራጠሩ ያደርጋቸዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከእስራኤል ጋር ሊያደርጉት ከሚችለው ውጊያ የሚያዘናጋቸው ጥልቅ ውስጣዊ ምርመራ እንደሚያደርጉ እጠብቃለሁ” ብለዋል።
የሄዝቦላህ እና የእስራኤል ግጭትስ ይባባስ ይሆን?
ሄዝቦላህ በአካባቢው ከእስራኤል ጋር በዓይነ ቁራኛ ከምትተያየው ኢራን ጋር በአጋርነት ይሠራል። ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ለወራት የዘለቀ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ጦርነት ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፣ በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ላይ በተደጋጋሚ የሮኬት እና የሚሳኤል ተኩስ ልውውጥ አድርጓል።
አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ድንበር ተሻጋሪ ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካታ ነዋሪዎች ከድንበር አካባቢ ተፈናቅለዋል።
ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት የእስራኤል ካቢኔ ነዋሪዎችን ወደ ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በሰላም ለመመለስ ይፋዊ ግብ ካስቀመጠ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጉብኝት ላይ ለሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን እስራኤል “ደኅንነቷን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ ታደርጋለች” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት ሄዝቦላህ የቀድሞ ባለሥልጣንን ለመግደል ያደረገውን ሙከራ ማክሸፉን የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት ኤጀንሲ ተናግሯል።
ውጥረቱ እየቀጠለ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ወደ ሙሉ ጦርነት ላለማለፍ ቀዩን መስመር ላለማለፍ ሲጥሩ እንደነበር ታዛቢዎች ይገልጻሉ። ሄዝቦላህ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ መዛቱን ተከትሎ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ ይችላል የሚል ስጋት ግን አለ።