ሁለት አንጋፋ ፖለቲከኞች ለፕሬዝዳንትነት የተፋጠጡበት የኬንያ ምርጫ ወዴት ያመራል?

ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ

ባለፈው ማክሰኞ ለብሔራዊ ምርጫ ድምጻቸውን የሰጡት ኬንያውን ውጤቱን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። የድምጽ ቆጠራው አሁንም እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለፕሬዝዳንትንት የቀረቡት ዋነኛዎቹ ዕጩዎች በጠባብ የድምጽ ልዩነት እየተፎካከሩ ነው።

በአፍሪካ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት፣ የፍትሕ እና የምርጫ ሥርዓት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ካላቸው ጥቂት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኬንያ የሚካሄደው ምርጫ ውጤት ከአገሪቱ ባሻገር በአህጉሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረትን የሚያገኝ ነው።

22 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ በመራጭነት የተመዘገበበትና 14 ሚሊዮኑ ድምጹን በሰጠበት በዚህ ምርጫ ኬንያውያን ለፕሬዝዳንት፣ ለግዛቶች አስተዳዳሪዎች፣ የብሔራዊ እና የአካባቢያዊ ምክር ቤቶች አባላትን ለመምረጥ ድምጽ ሰጥተዋል።

ከዚህ መካከል ከፍተኛ ትኩረትን የሳበው ግን አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የሚደረገው ፉክክር ነው።

ይህ ፉክክር በዋናነት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በሆኑት ዊሊያም ሩቶ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የሚደረገው ፉክክር ከባድ እንደሚሆን ቀድሞም ተጠብቆ ነበር።

በሁለቱ ግዙፍ ፖለቲከኞች መካከል ያለው ፉክክር ግጭትን እንዳያስከትል የብዙዎች ስጋት ሲሆን፣ አስካሁን በነበረው ሁኔታ ግን ይህ ነው የሚባል የጎላ የፀጥታ ችግር በተፎካካሪዎቹ ደጋፊዎች መካከል አልተከሰተም።

ነገር ግን ድምጽ ተሰጥቶ ቆጠራው ከተጀመረ ሁለተኛው ቀን ቢሆንም እስካሁን ሩቶ እና ራይላ ከመራጮች ባገኙት ድምጽ ግልጽ የበላይነት ማግኘት አልቻሉም።

በምርጫው ድምጽ ከሰጡት መራጮች መካከል ወደ ግማሽ የሚሆነው ድምጽ የተቆጠረ ቢሆንም ልዩነታቸው ጠባብ የሚባል በመሆኑ ኬንያውያን ውጤቱን በጉጉት እየጠበቁ ነው።

ዊሊያም ሩቶ ድምጽ ሲሰጡ
የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ሩቶ ድምጽ ሲሰጡ

በዚህ ምርጫ ምን ይጠበቃል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በርካታ ሚሊዮኖች ለቀጣዩ አምስት ዓመታት አገራቸውን የሚመራውን ፕሬዝዳንት መርጠው ውጤቱን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበርም ምርጫ ከተደረገበት ማክሰኞ ነሐሴ 03 እስከ ቀጣዮቹ ሰባት ቀናት ድረስም የምርጫውን ውጤት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።

ነገር ግን በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ምን አይነት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለን እንጠብቅ?

የመጀመሪያው በምርጫው ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ግልጽ አሸናፊ ይኖራል። በዚህም አሸናፊው በቀጥታ ይፋ ይሆናል።

ይህም ማለት ከተሰጠው አጠቃላይ ድምጽ ውስጥ ከግማሽ በላይ እና ቢያንስ ከ47ቱ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ በ24ቱ ከተሰጠው ድምጽ 25 በመቶውን ማግኘቱን ካረጋገጠ ነው።

ይህም አከራካሪ የማይሆን ሲሆን ሌሎቹም ዕጩ ተወዳዳሪዎች አምነው መቀበል አለባቸው። አሸናፊው በቀላሉ በቀጥታ የሚለይ ከሆነ፣ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ባለው የመጀመሪያው ማክሰኞ መንበሩን ለመረከብ ቃለ መሃላ እና የሲመት ተግባር ይከናወናል።

ሌላኛው ሁኔታ ደግሞ አሸናፊው በምርጫ ኮሚሽኑ ቢነገርም ውጤቱ በፍርድ ቤት አከራካሪ የሚሆኑበት ነው።

ውጤቱ አከራካሪ ነው ከተባለ አሸናፊው በኮሚሽኑ ከተገለጸበት ዕለት አንስቶ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ቅሬታ አቅራቢዎች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አለባቸው። 

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም አቤቱታው በቀረበ በ21 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል። ፍርድ ቤቱ በዚህም ብያኔው ድሉን ያጸናል ወይም ውድቅ ያደርገዋል።

የምርጫውን ውድቅ የሚያደርገውም ከሆነ በ60 ቀናት ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ትዕዛዝ ያስተላልፋል።

ሌላኛው ከዚህ የምርጫ ውጤት የሚጠበቀው ኮሚሽኑ አሸናፊውን ፕሬዝዳንትን ያውጃል፣ ነገር ግን ተሸናፊው ዕጩ ፕሬዝዳንት አሸንፌያለሁ ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜ ነው።

በዚህ ሁኔታ የተመረጠው ፕሬዝዳንት ቃለ መሃላ እንዲፈጽም ይደረጋል። ሆኖም በዚህ ወቅት የተወሳሳሰቡ ነገሮች ሊከተሉ ይችላሉ።

በአውሮፓውያኑ በ2007 ከተደረገው ምርጫ በኋላ እንደታየው የፖለቲካ እና የብሔር ውዝግብ ባስነሳው ብጥብጥ ወቅት በርካታ ሕይወትን የፈጠረው አይነት ቀውስም ሊያስከትል ይችላል።

ሌላ ሊፈጠር የሚችለው ጉዳይ ደግሞ ግልፅ አሸናፊ አለመኖር ነው። ይህም ማለት ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ከግማሽ በላይ የመራጮችን ድምፅ ባያገኙና ቢያንስ ከ47 ክልሎች ውስጥ በ24ቱ ከተሰጡት ድምጾች 25 በመቶውን ማግኘት ካልቻሉ ነው።

ይህ የሚፈጠር ከሆነ በሁለቱ ግንባር ቀደም ዕጩዎች መካከል ሁለተኛ ዙር ምርጫ መደረግ አለበት። ይህም ምርጫ የሚከናነው የመጀመሪያው ምርጫ ከተከናወነ ከ30 ቀናት በኋላ ይሆናል።

ፕሬዝዳንት ኬንያታ እና ራይላ ኦዲንጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፕሬዝዳንት ኬንያታ እና በራይላ ኦዲንጋ መካከል ሰላም ያወረደው መጨባበጥ

የቀደመው ምርጫ

ከአምስት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአሁኑ ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ እንዲሁ እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ድምጽ ሲፎካከሩ ቆይተው በመጨረሻ ላይ ሥልጣን ላይ የነበሩት ኬንያታ ማሸነፋቸው መታወጁ ይታወሳል።

ነገር ግን ውጤቱ ላይ ጥያቄዎች ተነስተው በአንዳንድ ቦታዎችም የተቃዋሚው ፖለቲከኞች ደጋፊዎች ወደ ጎዳና በመውጣት ግጭቶች ተከስተው ነበር።

አሸናፊው የበላይነቱን ሲገልጽ ተሸናፊው ግን ማጭበርበር ተፈጽሟል በሚል ውጤቱን ባለመቀበል አገሪቱ ውጥረት ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ፖለቲከኞቹም ተቃውሞውና ውጥረቱ ጋብ እንዲል ደጋፊዎቻቸውን ሲጠይቁ፣ በምርጫው አሸናፊ ነኝ ያሉት ተቃዋሚው ራይላ ደግሞ አቤቱታቸውን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው ሄዱ።

ኬንያ አሉኝ ብላ ከምትኮራባቸው አገራዊ ተቋሞቿ መካከል አንዱ የሆነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቷ የቀረበለትን አቤቱታ የምርጫውን ያህል ጉጉትን በፈጠረ ሁኔታ ሲመለከት ቆይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ፍርድ ቤቱ ከሁለቱም ወገኖች የቀረቡለትን አቤቱታዎችና ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ በሥልጣን ላይ ያለው ፕሬዝዳንት ያሸነፈበትን የምርጫ ውጤት ውድቅ በማድረግ ምርጫው እንዲደገም ወሰነ።

አፍሪካም ዓለምም ውሳኔውን በአድናቆት ተመለከቱት፣ አሸናፊነታቸው ታወጆ የነበሩት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብለው ለድጋሚ ምርጫ መዘጋጀታቸውን ጀምረው ነበር።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በድጋሚ በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሁን ሁለተኛ አምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው አጠናቀው የሚሰናበቱት ኡሁሩ ኬንያታ በድጋሚ ማሸነፋቸው ተረጋገጠ።

ነገር ግን ራይላ የሁለተኛው ዙር ሽንፈታቸውንም በፀጋ ባለመቀበል ሕጋዊው ፕሬዝዳንት ነኝ በማለት በይፋ ቃለ መሐላ አስከመፈጸም ደርሰው ነበር።

ኋላ ላይ ግን ፕሬዝዳንቱ እና ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ተቀራርበው ሰላም አውርደው አሁን አጋር አስከመሆን ደርሰዋል።

በዚህ በአሁኑ ምርጫም ፕሬዝዳንት ኬንያታ ከምክትላቸው ሩቶ ይልቅ ለተቃዋሚው ራይላ ድጋፋቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።