በትግራይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 20 ሰዎች መቁሰላቸው ተነገረ

ጠመንጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትግራይ ክልል መዲና መቀለ አቅራቢያ በምትገኘው ሰሐርቲ ወረዳ፣ ረቡዕ፣ የካቲት 12/ 2017 ዓ.ም ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 20 ሰዎች መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሰሐርቲ ወረዳ፣ አዲስ አለም ቀበሌ አጽገብታ መንደር የተፈጸመውን ይህንን ጥቃት አውግዞ፣ ፖለቲካዊ አላማ እንዳለው በመግለጽ፤ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት አዛዦችን በድርጊቱ ከሷቸዋል።

"በሰሐርቲ ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ኃይልተጠቅሞ የቀበሌውን መዋቅር ለማፍረስ የሚደረግ ህጋዊ ያልሆነ ተግባር ማሳያ ነው" ብሏል።

"በዛሬው ዕለት [የካቲት 12/ 2017ዓ.ም.] የትግራይ ሰራዊት የተወሰኑ አመራሮች በየካቲት 11 ዋዜማ [የትግራይ ወጣቶች በደርግ አገዛዝ ላይ የትጥቅ ትግል ያነሱበት ወቅት] የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅርን አላግባብ እያፈረሱ መሆናቸውን ታዝበናል" ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሐሙስ፣ የካቲት 13/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት፤ ፓርቲው በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል እና በምክትል ሊቀመንበሩ ጌታቸው ረዳ በሚመሩ ቡድኖች ተከፍሎ እየተወዛገበ ይገኛል።

ለወራት በገለልተኝነት የቆዩት የትግራይ ሰራዊት አዛዦች አብዛኞቹ በደብረጽዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ መለዮ የለበሱ 10 ታጣቂዎች መጀመሪያ ላይ ወደ ቀበሌው የመጡት "ችግር እንዳለ ከተነገራቸው" በኋላ እንደሆነ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ፤ ተመልሰው ሄደው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተጨማሪ ታጣቂዎችን ጨምረው 30 ሆነው እንደተመለሱ እና የአዲስ ዓለም ቀበሌ አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ መለስ አስገደ ማህተሙን እንዲያስረክቡ እንዳስገደዷቸው ይናገራሉ።

የአጽገብታ መንደር ነዋሪ አቶ ነጋሲ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ታጣቂዎቹ "በነዋሪው ላይ እንግልት እና ማሸበር ፈጽመዋል" ብለዋል።

"ሳይታሰብ መጥተው ማህተሙን ለመንጠቅ ሞከሩ። የአካባቢው ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች ተሰብስበው ህዝቡ ያስተዳደሩናል ብሎ መርጧቸው እያለ 'ምን እያደረጋችኋቸው ነው?' ቢሏቸውም ሊሰሙ አልቻሉም" ሲሉ አስረድተዋል።

የቀበሌው የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ጸጉ በርሄ በበኩላቸው፤ ግጭቱ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረው ታጣቂዎች እናግባባችኋለን በማለት ማህተሙን እንደወሰዱት ገልጸዋል።

"በወቅቱ መኖሪያ ቤቴ ነበርኩኝ። ቤቴ መጡና ማህተም አምጪ አሉኝ " የሚሉት ጸጉ፤ በህዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማለት መግባባት ላይ ለመድረስ ጥረት መደረጉን ያስረዳሉ።

ከህዝቡ ጋር መግባባቱን ትተው ታጣቂዎቹ ማህተሙን ይዘው ለመሸሽ ሲሞክሩ ይህንን ለማስቆም ጥረት ባደረጉ ግለሰቦች ላይ ተኩስ መከፈቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተከፈተው ተኩስ 20 የሚጠጉ ነዋሪዎች እንደተጎዱ እና አንድ በጽኑ የተጎዱ ግለሰብ ወደ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እንደተወሰዱ ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የደቡብ ምስራቅ ትግራይ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጸጋጠወ ገብረተኽለ እንደተናገሩት፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው "ማህተም አስረክቡ " በሚል ውዝግብ እንደሆነ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን አስረድተዋል።

ታጣቂዎቹ ደንጎላት ከተባለ አካባቢ የመጡ የትግራይ ኃይል አባላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ "የትግራይ ሰራዊት የህዝቡን ህልውና ለማስጠበቅ የተሰለፈ ኃይል እንጂ የተወሰነ ቡድን የስልጣን ጥማት ለማርካት እንዳልሆነ እየታወቀ ሳለ ከስርአት ውጪ በሆነ መንገድ የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር ለማፍረስ በፍፁም ሊሰማራ አይገባም" ብሏል።

"ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ህዝባችን እንደ ሀገር ልንወጣው ወደማንችልበት ከባድ ቀውስ እንደምንገባ ሊረዱ ይገባል" ሲልም አሳስቧል።

አክሎም፤ "የትግራይ ሰራዊት እነዚህን አንዳንድ የሰራዊት አመራሮች እየፈጸሙት ያለውን የህግ ጥሰት በሚገባ ተረድተው፤ ወደ ስህተት መንገድ እየገቡ ከመንግሥት እና ህዝብ ተቃራኒ የቆሙ አካላት አደብ እንዲገዙ እርምጃ እንዲወስድ" የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።

የትግራይ ሠራዊት አዛዦች በቅርቡ ባወጡት መግለጫ በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን ይህም አጋርነታቸው በዶ/ር ደብረጽዮን ለሚመራው ቡድን መሆኑን በተዘዋዋሪ አመልክተዋል።

አዛዦቹ፤ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የሠራዊቱ አመራሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው ሲሉ ወቀሳቸውን አሰምተዋል። "የተዳከመ" እና "ተልዕኮውን የዘነጋ" ሲሉ የጠሩትን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማጠናከር አመራሮቹ ተነስተው በሌሎች መተካት እንዳለባቸውም አሳስበው ነበር።

የፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአዲስ እንዲዋቀር ወስነናል ያሉን የትግራይ ሠራዊት አዛዦች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል" ሲል መክሰሱ ይታወሳል።

የሠራዊት አዛዦቹ የሰጡት መግለጫ "የጦርነት አዋጅ እና ሥርዓት አልበኝነት" የሚያስከትል በመሆኑ የትግራይ የፀጥታ አባላት ሁኔታውን "ልብ ብለው በመገንዘብ አትኩሮት እንዲነፍጉት እና ከዚህ ውጪ የሚመጣው ማንኛው ዓይነት ትዕዛዝን ተግባራዊ እንዳያደርጉ እናሳስባለን" ሲል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል።