ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ባይደን በሳዑዲ ጉብኝታቸው ስለተገደለው ጋዜጠኛ ማንሳታቸውን ተናገሩ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋር በተገናኙበት ወቅት ስለጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ማንሳታቸውን ተናገሩ።
ባይደን ቀደም ሲል በሰብዓዊ መብት አያያዟ ምክንያት እንድትነጠል እንደሚያደርጉ ሲያስጠነቅቋት ከነበረችው ሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በሳዑዲ ጉብኝት እያደረጉ ባለበት ወቅት እንደተናገሩት ከሦስት ዓመት በፊት ቱርክ ውስጥ የተፈጸመው የጋዜጠኛው ግድያ “ዩናይትድ ስቴትስ እና እኔ እራሴ ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም ሁለቱ አገራት በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረስ እንደቻሉ አመለክተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ጥቅምት ወር ላይ መቀመጫውን አሜሪካ አድርጎ ይሰራ የነበረው የሳዑዲ ዜጋ የሆነው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ቱርክ ኢስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ከተገደለ በኋላ፣ ፕሬዝዳንት ባይደን ወደ ሳዑዲ ጉብኝት ማድረጋቸው ከፍተኛ ትችትን አስከትሎባቸዋል።
የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት የሳዑዲው ልዑል የጋዜጠኛውን ግድያ አዘዋል በማለት ስለሚከሷቸው የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ግድያውን ችላ የማለት ምልክት ነው በሚል ነው የተወቀሱት።
ልዑሉ ግን በግድያው ውስጥ እጃቸው እንደሌለበት ሲያስተባብሉ የሳዑዲ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ በአገሪቱ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሕገ ወጦች የፈጸሙት ግድያ ነው ይላል።
“በውይይታችን መጀመሪያ ላይ የኻሾግጂን ግድያ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያሰብኩትንና አሁን የማስበውን ግልጽ አድርጌላቸዋልሁ” ሲሉ ከሳዑዲ ባለሥልጣንት በኋላ ባይደን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ግድያውን በተመለከተ “በግላቸው ተጠያቂ እንዳልሆኑ” እንደነገሯቸው አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ፕሬዝዳንቱም “እጃቸው አለበት ብለው ያስቡ እንደነበር” ለልዑሉ ምላሽ እንደሰጡ ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከልዑል ሰልማን ጋር ሲገናኙ የሚያሳየውን ፎቶ በመጥቀስ የሟቹ ጋዜጠኛ እጮኛ ሃቲስ ሲንጊዝ ባይደንን ተችታለች።
ሲንጊዝ የሁለቱን መሪዎች ፎቶ አያይዛ ትዊተር ላይ ባሰፈረችው መልዕክት “ለግድያው ተጠያቂነት እንዲኖር አደርጋለሁ ያሉት ይህንን ለማድረግ ነው? ቀጣዩ የልዑሉ ሰለባ የሚሆነው ግለሰብ ደም በእጅዎ ላይ ነው” ስትል የኻሾግጂ እጮኛ ፕሬዝዳንት ባይደንን ወቅሳለች።
ኻሾግጂ ሲጽፍበት የነበረው ዋሽንግትን ፖስት ጋዜጣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬድ ሪያንም፣ ባይደን ከልዑሉ ጋር የተለዋወጡት ሰላምታ ተጠያቂነትን ችላ በማለት ልዑሉ ከወንጀላቸው ለመንጻት የሚፈልጉትን መልዕክት ያስተላላፈ “አሳፋሪ” ድርጊት ነው ብለውታል።
ከኻሾግጂ ግድያ በተጨማሪ ሁለቱ መሪዎች ሳዑዲ አረቢያ ዋነኛዋ አምራች ስለሆነችውና ዋጋው እየተወደደ ያለውን ነዳጅ በተመለከተ በመወያየት፣ በቀጣይ ሳምንታት የነዳጅ ዘይት ገበያውን ለማረጋጋት ሳዑዲ ስለምትወስደው እርምጃም ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ሳዑዲ አረቢያ ከዚህ በፊት ፈቅዳ የማታውቀውን ከአስራኤል እና ወደ አስራኤል ለሚበሩ አውሮፕላኖች የአየር ክልሏል ክፍት ማድጓን ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።