አሜሪካ ከሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያለውን መንገድ በጀማል ኻሾግጂ ስም ሰየመች

ዋሽንግተን የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት የሚገኘው መንገድ ጀማል ኻሾግጂ በሚል ተሰየመ።

ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ በሳዑዲ አረቢያ የደኅንነት አባላት ቱርክ ውስጥ ከተገደለ በኋላ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል።

የአሜሪካ ርዕሰ ከተማ አስተዳዳሪ ስያሜው ጀማል ኻሾግጂ መንገድ መባሉ የጋዜጠኛው ሞት “እንዳይሸፋፈን ያግዛል” ብለዋል።

የአሜሪካ ደኅንነት ግድያውን በተመለከተ በደረሰው ድምዳሜ ላይ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ግድያው እንዲፈጸም ውሳኔ ሰጥተዋል። ልዑሉ ግን ያስተባብላሉ።

በሚቀጥለው ሳምንት ልዑሉ ከአሜሪካው ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ይመክራሉ።

የመንገዱ ስያሜ በጋዜጠኛው ስም መሆኑን በማስመልከት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

“ከዚያ አጥር ጀርባ የተደበቁት ሰዎች በየቀኑ፣ በየሰዓቱ ይህ የጀማል ኻሾግጂ መንገድ መሆኑን እንዲያስታውሱ ለማድረግ ያለመ ነው” ያሉት የዴሞክራሲ ፎር ዘ አረብ ዎርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳራ ሊያ ናቸው።

ድርጅቱ በጀማል ኻሾግጂ የተቋቋመ ቡድን ነው። ሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ መቀመጫውን አሜሪካ እድርጎ የነበረ ሲሆን ለዋሽንግተን ፖስትም ይጽፍ ነበር።

ጋዜጠኛው እአአ በ2018 ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ውስጥ በአገሪቱ ደኅንነት አባላት ተገድሏል።

የአሜሪካ ደኅንነት ጉዳዩን በቀጥታ ከልዑል ሞሐመድ ጋር አያይዘውታል። ልዑሉ ግን በግድያው ውስጥ እጃቸው እንደሌለበት አስተባብለዋል። የሳዑዲ ዐቃቤ ሕጎች ገዳዮቹ “ሕገ ወጥ” ወኪሎች ናቸው ሲሉ ይከሳሉ።

ግድያው ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ልዑሉም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገለሉ አድርጓል።

የዴሞካራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን በሚፎካከሩበት ወቅት ፕሬዝዳንት ባይደን “[ሳዑዲ አረቢያ] ለሠራችው ሥራ ዋጋዋን እንድታገኝ አደርጋለሁ” ሲሉ በግድያው ዙሪያ ተናግረው ነበር።

ማክሰኞ ዕለት ዋይት ሐውስ እንዳስታወቀው ባይደን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚኖራቸው ጉብኝት ከልዑል ሞሐመድ ጋር ፊት ለፊት ይገናኛሉ።

የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥለጣን እንዳሉት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከውይይቶቹ አጀንዳዎች አንዱ ነው። ሌሎች ደግሞ ውይይቱ ሳዑዲ ምንም መሻሻል ሳታሳይ ዕውቅና ሊሰጣት ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ዋሽንግተን በተገደሉ ሰዎች ስም ከኤምባሲዎች ፊት ለፊት መንገድ ስትሰይም ጀማል ኻሾግጂ የመጀመሪያው መንገድ አይደለም።

እአአ በ2015 በክሬምሊን ለተገደለው ቦሪስ ኔምሶቭ መታሰቢያ እንዲሆን የከተማዋ አስተዳደር የሩሲያ ኤምባሲ ፊት ለፊት የሚገኘውን መንገድ በግለሰቡ ስም ሰይሞታል።