በዩክሬን የድሮን ጥቃት ምክንያት የሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያዎች መዘጋታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩክሬን ለሁለት ተከታታይ ምሽቶች በግዛቷ ውስጥ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሟን ሩሲያ ገለጸች።
የሞስኮ አራቱም ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቱን ተከትሎ ለሰዓታት መዘጋታቸው ተገልጿል።
የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌ ሶብያን እንዳሉት፣ 19 ከተለያየ አቅጣጫ የተወነጨፉ የዩክሬን ድሮኖች ሰማይ ላይ ሳይደርሱ ወድመዋል።
የተወሰኑት ድሮኖች ግን ዋነኛ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዳረፉ እና በሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።
ዩክሬን ጥቃቱ መፈጸሙን ባታረጋግጥም የኪቭ ከንቲባ በበኩላቸው ሩሲያም ምሽት ላይ የድሮን ጥቃት መሰንዘሯን ገልጸዋል።
የሩሲያ ፔንዛ እና ቮሮኔዝ ከተሞች ከንቲባዎችም የድሮን ጥቃት ዒላማ ሆነናል ብለዋል።
ያልተረጋገጡ የሩሲያ ወታደራዊ ድረ ገጾች እንደሚሉት በደቡብ ሞስኮ የሕንጻ መስኮቶች ተሰባብረዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰኞ 26 የዩክሬን ድሮኖችን እንዳከሸፈ አስታውቋል።
ዩክሬን ባለፈው ወር ባደረሰችው የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች ሞስኮ ውስጥ ተገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዩክሬን ወደ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ለመግባት እየሞከረች እንደሆነ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ከሁለት ወር በፊት ሩሲያ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን አስታውቃለች። ዩክሬን ግን አሁንም በሥፍራው ወታደሮች እንዳሏት ትገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩክሬን ባደረሰቸው ጥቃት ሳቢያ ያሳለፍነው ሰኞ ዕለት በኩርስክ በሚገኘው ሪልስክ ከተማ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መቋረጡን አገረ ገዢው አሌክሳንደር ኪንስቲን ተናግረዋል።
በጥቃቱም ሁለት ታዳጊዎች መጎዳታቸውንም አክለዋል።
ቢቢሲ ያላረጋገጣቸው የሩሲያ ወታደራዊ ድረ ገጾች እንደሚሉት ዩክሬን በሚሳዔል እና በቦምብ ድንበር አሻግራ ጥቃት ፈጽማለች።
"ጠላቶቻችን በሮኬት ድልድይ አፍርሰውብናል። ጠዋት ላይ ወታደሮች ጥቃትም ሰንዝረዋል። በወታደር የተሞሉ ተሽከርካሪዎች ጉዞ ጀምረዋል። ድንበር ላይ ከፍተኛ ውጊያ ነው ያለው" ሲል አንድ የድረ ገጽ ጦማሪ ገልጿል።
ዩክሬን ባወጣችው መግለጫ "በኩርስክ ግዛት ኦፕሬሽን ከጀመርን ከዘጠኝ ወራት በኋላ በሥፍራው ያሉት ወታደሮች እንቅስቃሴ ቀጥለዋል" ብላለች።
ከሩሲያ በኩል ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም ወታደራዊ ድረ ገጾች በሁለቱም ወገን ያለውን ፍጥጫ አመልክተዋል።
ከዩክሬን ሰሜን ምሥራቃዊ ድንበር 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ሱሚ ነዋሪዎች በአፋጣኝ እንዲወጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
ዩክሬን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በኩርስክ ማድረሷ ይታወሳል።
ሱሚ ከተማን ለመጠበቅ እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ የከለላ ቦታ ለማግኘት ስትል ጥቃቱን የፈጸመች ሲሆን፣ በቀጣይ ለሚኖሩ ውይይቶች እንደ አንድ የመደራደሪያ ነጥብ ለመያዝም ትፈልጋለች።












