የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይ ሕዝብን ይቅርታ ጠየቀ

አቡነ ጴጥሮስ እና ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ

የፎቶው ባለመብት, mahbere kidusan/fb

የምስሉ መግለጫ, አቡነ ጴጥሮስ እና ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ ይቅርታ ጠየቀ።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ባለፉት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ በተመለከተ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ በጦርነቱ ወቅት የቤተክርስቲያኗን አባቶች እና ምዕመናንን ደኅንነት በመተመለከተ አስፈላጊውን ሁሉ ባለማድረጉ ይቅርታ መጠየቁን ገልጿል።

ለሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅባትን አላደረገችም በሚል በትግራይ አባቶች እና ምዕመናን በኩል በጥብቅ ስትተች ቆይታለች።

ይህንንም ተከትሎ ቅሬታ የገባቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶሱ በመለየት የተናጠል ቤተ ክህንት ለማቋቋም ወስነው፣ ጳጳሳትን እንደሚሾሙ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እና ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባት እና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን እና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋ እንዲሁም ባለማጽናናቷ” ይቅርታ እንደምትጠይቅ ሲኖዶሱ ገልጿል።

መግለጫው አክሎም ቤተ ክርስቲያኒቱ “ጦርነቱ ቁሞ ሰላም ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ፣ በዚሁም የተነሳ በቤተ ክርስቲያኗ እና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታ እና አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል” ብሏል።

ይህ የቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታ የቀረበው የቤተ ክርሰቲያኗ መሪዎች በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ለመነጋገር እና ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለመሻት በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደዚያው እንደሚያመሩ ከተገለጸ በኋላ ነው።

በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ጥንታዊ እና ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ይገኛሉ።

በትግራይ ያሉ የእምነቱ መሪዎች በተዳጋጋሚ እንዳሉት በጦርነቱ ወቅት በርካታ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳለው በጦርነቱ ወቅት ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ እና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አባቶች እና ምዕመናንን ለመደገፍ የሚጠበቅበትን ባያደርግም፣ የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለጦርነቱ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በውስን አጋጣሚዎች በትግራይ ውስጥ ስለተካሄደው ጦርነት እና ስለደረሱ ጉዳቶች አንስተው ተናግረዋል።

ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተዛምቶ በነበረው ደም አፋሳሹ የሁለት ዓመታት ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ይነገራል።

ባለፈው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረሰ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ መቆሙ ይታወሳል።