ትራምፕ ቢቢሲ ላይ የአምስት ቢሊዮን ዶላር የስም ማጥፋት ክስ ከፈቱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲን በስም ማጥፋት ከሰሱ።

ቢቢሲ ያስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ ከተደረገው አርትኦት ጋር በተያያዘ የ5 ቢሊዮን ዶላር ክስ መክፈታቸው ይፋ ተደርጓል።

ቢቢሲ ስሜን አጥፍቷል፣ የንግድ ሕግንም ጥሷል ሲሉ ትራምፕ ተቋሙን በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ከስሰዋል።

የፓኖራማ ዘጋቢ ፊልም ከተደረገበት አርትኦት ጋር በተያያዘ የተከፈተው ክስ የ5 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ቢቢሲ ትራምፕን ይቅርታ ቢጠይቅም ካሳ ለመክፈል አልተስማማም። ቢቢሲ "መድልዎና ስም ማጥፋት" ተፈጽሟል የሚለውን ክስም አልተቀበለም።

የትራምፕ ጠበቆች ቢቢሲ የፕሬዝዳንቱን ስም እንዳጠፋ እና "ሆነ ብሎ፣ ተንኮል አዘል እና አሳሳች በሆነ መንገድ ንግግራቸውን እንዳቀናበረ" ተናግረዋል።

ቢቢሲ ስለቀረበበት ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

የአሜሪካ ምርጫ በ2024 ከመካሄዱ አስቀድሞ ዘጋቢ ፊልሙ በዩናይትድ ኪንግደም ተላልፏል። ባለፈው ወር ትራምፕ ቢቢሲን እንደሚከስሱ ገልጸዋል።

"መክሰስ አለብኝ። አጭበርብረዋል፤ ከአፌ የወጡትን ቃላት ለውጠዋል" ብለዋል።

እአአ ጥር 6/2021 በካፒቶል ሂል ነውጥ ከመነሳቱ አስቀድሞ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን። ጀግና ሴናተሮች እና የኮንግረስ አባላትን እናበረታታለን" ብለዋል።

ይህንን ተናግረው ከ50 ደቂቃዎች በኋላ "እንታገላለን፤ በእጅጉ እንታገላለን" ሲሉ ይደመጣሉ።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ሁለቱ ንግግሮች አንድ ላይ ሆነው "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን። ጀግና ሴናተሮች እና የኮንግረስ አባላትን እናበረታታለን. . . እንታገላለን፤ በእጅጉ እንታገላለን" በሚል ቀርቧል።

የተደረገው አርትኦት "ነውጥን ለማነሳሳት ቀጥተኛ ጥሪ ያደረጉ በማስመሰል የተሳሳተ ትርጉም" ሊሰጥ እንደሚችል ቢቢሲ አምኗል። ሆኖም ግን የስም ማጥፋት ክስ የሚያስከትል መሆኑን አልተስማማበትም።

ያለፈው ኅዳር ሾልኮ የወጣ የቢቢሲ መረጃ እንደሚጠቁመው ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተደረገው አርትኦት ተተችቷል። የቢቢሲ ዋና ኃላፊ ቲም ዴቪ እና የዜና ክፍል ኃላፊ ዴቦራ ቱርነስ ከሥራ እንዲለቁም ምክንያት ሆኗል።

ትራምፕ ቢቢሲን ከመክሰሳቸው በፊት የቢቢሲ ጠበቆች ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠበቆቹ እንዳሉት ከአርትኦቱ ጀርባ አንዳች ደባ ወይም ሴራ ካለመኖሩም ባሻገር ዘጋቢ ፊልሙ ከተላለፈ በኋላ ትራምፕ በድጋሚ በመመረጣቸው ፕሬዝዳንቱ ላይ ያስከተለው ጉዳት የለም።

ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙን በአሜሪካ የማስተላለፍ መብት እንደሌለው እና በአሜሪካ ዘጋቢ ፊልሙን እንዳላስተላለፈም ጠበቆቹ ተናግረዋል።

ዘጋቢ ፊልሙ በአይፕለየር ላይ የሚገኝ ቢሆንም በዩኬ ያሉ ተመልካቾች ብቻ ናቸው ማየት የሚችሉት።

የትራምፕ ጠበቆች በበኩላቸው ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙን ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ የሚችልበት ስምምነት እንዳለው ጠቅሰዋል።

ሦስተኛ ወገን የሆነ ተቋማት ፊልሙን በዩኬ ማሳየት እንደሚችሉ የትራምፕ ጠበቆች ቢናገሩም ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠም።

በተጨማሪም የፍሎሪዳ ነዋሪዎች ቪፒኤን ተጠቅመው ፊልሙን አይተው ሊሆን እንደሚችል የትራምፕ ጠበቆች ገልጸዋል።