ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ካሳ ሊከፍላቸው ፈቃደኛ ባልሆነው ቢቢሲ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ክስ ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ተናገሩ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ንግግራቸውን ቆርጦ ያቀረበበትን መንገድ በተመለከተ ይቅርታ ቢጠይቅም ካሳ ሊከፍላቸው ፈቃደኛ ባልሆነው ቢቢሲ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናገሩ።
ትራምፕ አርብ ማታ በፕሬዝዳንታዊው አውሮፕላን 'ኤር ፎርስ ዋን' ውስጥ ለጋዜጠኞች ምላሽ በሰጡበት ጊዜ፤ "ምናልባት የሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክስ እንመሰርትባቸዋለን" ብለዋል።
ቢቢሲ፤ ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ ጥር 6/2021 ያደረጉትን ንግግር ባለፈው ዓመት በተላለፈ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ በተካተተበት ወቅት ተቆርጦ የቀረበበት መንገድ በተመለከተ ሐሙስ ዕለት ይቅርታ ጠይቋል።
ንግግራቸው የቀረበበት መንገድ ባልታሰበበት መልኩ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአመጻ ድርጊት እንዲፈጸም ቀጥታ ጥሪ እንዳደረጉ ያስመለሰ ስህተት" እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጿል። ዘጋቢ ፊልሙ በድጋሚ እንደማይተላለፍም አክሏል።
ቢቢሲ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ቢጠይቅም ለፕሬዝዳንቱ ካሳ እንደማይከፍል አስታውቋል። ቢቢሲ ይህንን መግለጫ ያወጣው የትራምፕ ጠበቆች ክስ እንደሚመሠርቱ ከገለጹ በኋላ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ የሕግ ቡድን ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙን የማያወርድ፣ ይቅርታ የማይጠይቅ እና ካሳ የማይከፍል ከሆነ ዶክመንተሪው ላደረሰው ጉዳት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ እንደሚመሠርቱ አስጠንቅቀው ነበር።
ትራምፕ ጋዜጠኞችን ባነጋገሩበት ወቅት ሊወስዱ ስላሰቡት ሕጋዊ እርምጃ ሲያስረዱ "ማድረግ ያለብኝ ይመስለኛል" ብለዋል። "አጭበርብረዋል። ከአፌ የወጡትን ቃላት ቀይረዋል" ሲሉም ወንጅለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ከትራምፕ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ ያረቡ ቢሆንም አሜሪካው ፕሬዝዳንት ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አለማንሳታቸውን ገልጸዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ለስታርመር እንደሚደውሉም ተናግረዋል።
አርብ ምሽት በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት በሚገኙ የፌደራል እና የክልሉ ፍርድ ቤቶች ይፋዊ የመዝገብ ቋቶች ላይ የተደረገ አሰሳ እስካሁን ድረስ ክስ እንዳልተመሰረተ አሳይቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አውሮፕላን ውስጥ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት በተቀረጸ ቃለ መጠይቅ ላይ ቢቢሲን የመክሰስ "ግዴታ" እንዳለባቸው ተናግረዋል። "[ክስ መመሥረቱን] የማታደርገው ከሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ በድጋሚ እንዳይፈጠር ማስቆም አትችልም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትራምፕ በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ ንግግራቸው ተቆርጦ የቀረበበትን መንገድ "ከካማላ [ጊዜው] በባሰ" ሁኔታ "እጅግ መጥፎ" ሲሉ ገልጸውታል።
ትራምፕ በማነጻጸሪያነት የጠቀሱት በ2024 ምርጫ ተፎካካሪያቸው የነበሩት የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ቃለ መጠይቅ "የዴሞክራቶችን ምርጫ የማሸነፍ ዕድል ከፍ ለማድረግ" በሚሆን መልኩ ኤዲት ተደርጓል በሚል አቅርበውት የነበረውን ክስ ነው።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤት የሆነው ፓራማውንት ኩባንያ 16 ሚሊዮን ዶላት በመክፈል ክሱን ለመቋጨት ተስማምቷል።
ትራምፕ ከቢቢሲ ጋር እሰጣገባ ውስጥ የገቡት የመገናኛ ብዙኃን ተቋሙ ከአምስት ዓመት በፊት ያደረጉትን ንግግር አካትቶ ባለፈው ዓመት ባስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ምክንያት ነው።
ትራምፕ በ2021 ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን፣ እናም ጀግና ሴናተሮች፣ የኮንግረስ አባል ወንዶች እና ሴቶችን እናበረታታለን" ብለው ነበር።
ይህንን ካሉ ከ58 ደቂቃ በኋላ ደግሞ "እናም እንታገላለን። እስከመጨረሻው እንታገላለን" በማለት ተናግረዋል።
በቢቢሲው ዘጋቢ ፊልም ላይ የቀረበው የፕሬዝዳንቱ ንግግር "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን... አብሬያችሁ እሆናለሁ። እናም እንታገላለን። እስከመጨረሻው እንታገላለን" የሚል ነው።
የፕሬዝዳንቱ ንግግር ተቆርጦ የቀረበበት መንገድ ያስነሳው ውዝግብ የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ እና የዜና ክፍል ኃላፊዋ ዴብራ ተርነር ኃላፊነታቸውን እንዲለቅቁ ምክንያት ሆኗል።