የኤሎን መስክ ኩባንያ የነበረውን አብዛኛውን ቢትኮይን መልሶ ሸጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአንድ ዓመት በፊት በክሪፕቶከረንሲ ላይ ብዙ ኢንቨስት አድርጎ የነበረው የኤሎም መስክ ተቋም ቴስላ፤ ገዝቶት የነበረውን አብዛኛውን ቢትኮይን መልሶ ሸጠ።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ከነበረው ቢትኮይን 75 በመቶ የሚሆነውን መሸጡ ተገልጿል። ቴስላ የሸጠው ቢትኮይን እአአ 2021 መጨረሻ ላይ 2 ቢሊዮን ዶላር ያወጣ ነበር።
ኩባንያው ዋጋው እየወደቀ ካለው የክሪፕቶካረንሲ ኢንቨስትመንት እራሱን እያራቀ ነው ተብሏል። የቢትኮይን ዋጋ በጥቂት ወራት ውስጥ 50 በመቶ በላይ ዋጋውን አጥቷል።
ትልቅ ስም ካላቸው የክሪፕቶከረንሲ ወዳጆች መካከል የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ኤሎን መስክ ተጠቃሽ ነው።
ቴስላ እአአ 2021 መጀመሪያ ላይ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አውጥቶ ቢትኮይን ላይ ኢንቨስት ማድረጉ የክሪፕቶከረንሲ ዋጋን ከፍ አድርጎት ነበር።
ቴስላ ለሚሸጣቸው የኤሌክትሪክ መኪኖች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ እቀባላለሁ ብሎ የነበረ ቢሆንም፤ የቢትኮይን ግብይት የሚሳለጥበት ሥርዓት ከፍተኛ ኃይል እንደሚፈልግ በማስታወስ ቴስላ የከባቢ አየርን ለመጠበቅ ሲባል ቢትኮይንን እንደ ክፍያ አማራጭ ማቅረቤን ትቼዋለሁ ብሏል።
ቢትኮይን ከስምንት ወራት ገደማ በፊት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ አንድ ቢትኮይን 70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ጋር ተጠግቶ ነበር። ዛሬ ላይ ግን የአንድ የቢትኮይን ዋጋ ከ25 ሺህ ዶላር በታች እየተሸጠ ነው።
ቴስላ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ የሸመተውን ክሪፕቶከረንሲ መልሶ እንደማይሸጥ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤሎን መስክ በወቅቱ በትዊተር ጉጹ ላይ ጽፎ ነበር።
ኩባንያው ገዝቶት የነበረውን ቢትኮይን መልሶ እንደሸጠ ያሳወቀው የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ጊዜ ነው። ቴስላ ትርፋማነቴን ከጎዱት ምክንያቶች መካከል አንዱ ቢትኮይን ነው ብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኩባንያ የገበያ ድርሻ በ40 በመቶ ወርዷል።












