በከፍተኛ ሙቀት እየተገረፈች ባለችው አውሮፓ ኢትዮጵያውያን እንዴት እያሳለፉ ነው?

በአየር ማቀዝቀዣ (ፋን) ሥር የተቀመጠ ሕጻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውሮፓ በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እየተመታች ነው። በምዕራብ አውሮፓ የተከሰተው ኃይለኛ የሙቀት ማዕበል ወደ ሰሜናዊ ክፍልም እየተስፋፋ ነው። የሙቀት መጠኑም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛው ሙቀት ምክንያት ለሕዝባቸው ማስጠንቀቂያዎችን እየሰጡ ነው።

በርካቶችም ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሙቀት ማዕበሉን ተከትሎ ሰደድ እሳቶች እዚህም እዚያም ተከስተዋል፤ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል።

በፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል ፣ ስፔን እና ግሪክ በተቀሰቀሰው የሰደድ እሳት ሳቢያም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።

ሙቀቱ በከፋባቸው ዩኬ እና ፈረንሳይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙቀቱን እንዴት እያሳለፉት ነው?

በፈረንሳይ ነዋሪ የሆነው ላይነት ቢኒያም ሙቀቱ የተለማመድነው ነገር ነው ይላል።

ከ10 ዓመት በፊት ገደማ ለአንድ ሳምንት ያህል በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት በርካታ አረጋውያን ሕይወታቸውን እንዳጡ የሚያስታውሰው ላይነት፣ በአገሪቷ በሁሉም ቦታ የአየር ማቀዝቀዣ (ኤሲ) ስለሌለ ክስተቱን አስከፊ እንዳደረገው ይናገራል።

"ለእንደዚህ ዓይነት ሙቀት አገሩም ሰውም የተዘጋጀ አይደለም" ይላል።

ላይነት እንደሚለው በፈረንሳይ እንደ ዱባይና ጂዳ በሁሉም ቦታ የተገጠሙ የአየር ማቀዝቀሻዎች የሉም። ይህም በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ ለጉዳት እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል።

በመሆኑም የሰዎች ሕይወት መጥፋት ከመከሰቱ ባሻገር “የሆስፒታሎች መጨናነቅ፣ ጥላ ቦታዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የጋራ መገልገያ ቦታዎች ከሚገባው በላይ በሰዎች መሞላት ይታያል።" ሲልም ሰው ራሱን ለማዳን የተሻለ የሚለውን አማራጭ እየተጠቀመ እንደሆነም ያስረዳል።

ከዛሬ አስር ዓመት ወዲህም ፈረንሳይ ሙቀቱን ለመቋቋም ሕዝቡን እያዘጋጀች መጥታለች ብሏል።

በሰሜን ፈረንሳይ አካባቢ የሚኖረው ላይነት፣ ምንም እንኳን እርሱ ባለበት አካባቢ ሙቀቱ አስከፊ ባይሆንም፣ በደቡባዊ አካባቢ ግን ሙቀቱ እየበረታ እንደሆነ ይናገራል።

እርሱ እንደሚለው ሕንጻዎችና የአስፓልት መንገዶች በሚበረክቱበት ትልልቅ ከተሞች ሕንጻዎቹ ሙቀት ስበው ይዘው የመቆየት ባህርይ ስላላቸው ሙቀቱ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም ፈታኝ ነው።

ከትናንት በስቲያ ዩኬ ከፍተኛ የሙቀት መጠን አስመዝግባ እንደነበረ የሚናገረው ደግሞ የዩኬ ነዋሪው ዳዊት ዋቅጋሪ ነው።

"ባለፉት ቀናት ሙቀቱ እስከ 41 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር። ሂትሮ አየር ማረፊያ፣ ለንደን ፣ ካምብሪጅና አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የታየው ሙቀት በዚህ አገር ታሪክ የመጀመሪያው ነው” ይላል ዳዊት።

ሥራውን ከቤት ሆኖ እንደሚሠራ የሚናገረው ዳዊት፣ የሚያስፈልገውን እቃ ለመግዛት በወጣበት አንድ ሁለት ቀናት ሙቀቱ ከባድ እንደነበር ለማየት ችሏል።

“በርካታ ሰዎች የሚገለገሉበት የመጓጓዣ ሥርዓት ከመሬት በታች የተዘረጋ በመሆኑ በሌላ ጊዜም ሙቀት ቢስብም፣ አሁን ላይ ግን ለጤናም እጅግ አሳሳቢ ሆኗል። የሙቀት ስትሮክ (ሂት ስትሮክ) የሚያጋጥማቸው ሰዎች አሉ" ይላል።

ዳዊት እንደሚለው ከትናንት በስቲያ በዩኬ አምቡላንሶች ለበርካታ ሰዎች ለመድረስ ሥራ በዝቶባቸው ነበር የዋሉት። የእሳት አደጋዎችም ብዙ ቦታ ነበሩ።

የእሳት አደጋ መሥሪያ ቤትም ለንደን ውስጥ ከትናንት በስቲያ ሁኔታውን "ከባድ አደጋ " ሲል አውጆ ነበር።

ብዙ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውም ተነግሯል።

ከጫካ ውስጥ የተነሳ እሳት ወደ መኖሪያ ቤት ተዛምቶ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን መስማቱንም ዳዊት ተናግሯል።

በአውሮፓ አገራት ባለፉት ቀናት የተመዘገበው የሙቀት መጠን

ባለፉት ቀናት በርካታ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተመዘገበባቸው ሲሆን፣ በሰዎች ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል። የሙቀት መጠኑ ከዚህም በላይ ሊያይል እንደሚችል ስጋቶች አሉ።

  • በሰሜናዊ ስፔን 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠን ተመዝግቧል።
  • በርካታ የፈረንሳይ ክፍሎችም ከዚህ ቀደም አይተው የማያውቁትን ሙቀት ያስተናገዱ ሲሆን ምዕራባዊቷ ናንተስ ከተማ 42 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት አስተናግዳለች።
  • ዩናይትድ ኪንግደምም ሰኞ ዕለት በታሪኳ ከፍተኛ የተባለው ሙቀት ተመዝግቦባታል። በሱፎልክ ከፍተኛው 38.1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት የተመዘገበ ሲሆን፣ ሙቀቱ ከዚህ እንደሚሻገርም ትንበያዎች አመልክተዋል።
  • ግዙፎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጉግል እና ኦራክል በለንደን የሚገኙት የመረጃ ማዕከላቶቻቸው የአገልግሎት መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።
  • ኔዘርላንድስ የዓመቱን ከፍተኛ ሞቃታማ ቀን ሰኞ ዕለት መዝግባለች። በደቡብ ምዕራብ ዌስትዶርፕ ከታማ የሙቀቱ መጠን 33.6 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ነበር።
  • ቤልጂየም እና ጀርመን በሚቀጥሉት ቀናት 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ ሙቀት እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።
  • በስፔንና ፖርቹጋል ባለፉት ቀናት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ከሙቀት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል። በፖርቹጋል ያለው ሙቀት ሐሙስ ዕለት 47 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር።

ሙቀቱን እንዴት መቋቋም ይቻላል?

የየአገራቱ መንግሥታት ዜጎቻቸው ሙቀቱን ተከትሎ ከሚከሰቱ አደጋዎች ራሳቸው እንዲጠብቁ እያሳሰቡ ነው። ባሉበት ሆነውም ሙቀቱን እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው አበክረው እየመከሩ ነው።

ውጭ ያለው ሙቀት ወደቤት ውስጥ እንዳይገባ መስኮትና በሮችን መዝጋት፣ አረጋውያንን ነፋሻማ አየር ወዳለበት ቦታ መውሰድ፣ በቂ ውሃ መያዝና ቀዝቃዛ ውሃ መጠጣት፣ የአየር ማቀዝቀሻ (ፋን) መጠቀም፣ ከቤት አለመውጣት ከሚሰጡ ምክሮች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፈረንሳይ ነዋሪው ላይነትና የዩኬው ዳዊት እነዚህን ምክሮች በመተግበር የሙቀቱን ወጀብ ለመቋቋም ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከተማ ውስጥ ያለነው በዚህ መልኩ እያሳለፍን ቢሆንም በገጠራማ አካባቢዎች በእርሻ እና ደን ላይ በሙቀቱ ሳቢያ የሚነሳው እሳት ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ላይነት ተናግሯል።

የዩኬ ነዋሪው ዳዊት በበኩሉ “ምንም እንኳን ቤት ውስጥም ሙቀቱ ከባድ ቢሆንም፣ ቤት ውስጥ ሆኜ ሥራዬን እየሠራሁ ነው” ብሏል።

እንደዚህ ዓይነት የሙቀት ማዕበል በሚከሰትበት ወቅት ሰዎች ቀኑን እንደምንም ቢያሳልፉም ሌሊት ግን ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ይቸገራሉ። የጤና ባለሙያዎች በሙቀት ወቅት ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት የሚረዱ ነጥቦችን አጋርተዋል።