የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኮቪድ-19 ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኮቪድ-19 መያዛቸው በተደረገላቸው ምርመራ መረጋገጡን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ፕሬዝዳንት ባይደን በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ ያደረገው ዋይት ሐውስ፤ ፕሬዝዳንቱ "በጣም ቀላል" የበሽታው ምልክቶች ይታይባቸዋል ብሏል።
የ79 ዓመቱ ባይደን የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱ ሲሆን ሁለት ጊዜ የማጠናከሪያ ክትባቶችንም አግኝተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ፕሬዝዳንት ባይደን ፀረ ቫይረስ የሆነውን ፓክስሎቪድ የተባለውን መድኃኒት እየወሰዱ መሆኑም ተገልጿል።
የሰውነት በሽታን የመከላከያ ሥርዓት ቫይረሱን በሚዋጋበት ጊዜ፣ ይህ ፓክስሎቪድ የተባለው ፀረ ቫይረስ መድኃኒት የቫይረሱ መጠን በሰውነት ውስጥ እንዳይባዛ በማድረግ ዝቅተኛ መጠን እንዲኖረው አድርጎ ያቆያል።
ባለቤታቸው ቀዳማዊት ዕመቤት ጂል ባይደን ዴላዌር ግዛት ውስጥ እያሉ ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ እንደሌለባቸው ተረጋግጧል።
ጽህፈት ቤታቸው እንዳለው ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሐውስ ውስጥ እራሳቸውን አግልለው ኃላፊነቶቻቸውን መውጣታቸውን ይቀጥላሉ።
ባይደን በስልክ እና በዙም [ቪዲዮ] ስበሰባዎችን ይካፈላሉ ብሏል ቤተ - መንግሥታቸው።
የፕሬዝዳንቱ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ጄን ፒየር እንዳሉት የዋይት ሐውስ የሕክምና ቡድን፣ የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የቅርብ ንክኪ ለነበራቸው ሰዎች በሙሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መረጃ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በመጨረሻ ምርመራ ያደረጉት ማክሰኞ ዕለት ሲሆን በዚህም ቫይረሱ እንዳልነበረባቸው ታውቆ ነበር።
ከዚህ ቀደም በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሥልጣን ላይ ሳሉ በኮቪድ መያዛቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ በቅርቡ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ የወሰኑት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ህመም በርትቶባቸው ሕክምናቸውን በሆስፒታል መከታተል ግድ ብሏቸው ነበር።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ መሠረት አሜሪካ እስካሁን 90 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ሲሆን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።












