ዕድሜ ጠገቡ በእብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ 38 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

በዓለም በዕድሜ ቀደምት እና የተሟላ ነው የሚባለው በእብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ አሜሪካ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ ከ38 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠ።

ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኘው ሶዝቢስ አጫራች በኩል በ38.1 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በከፍተኛ ዋጋ በጨረታ የተሸጠ መጽሐፍ ሆኗል።

ይህ በእብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ከ1,100 ዓመታት በፊት የተዘጋጀ ነው ተብሎ ይታሰባል።

በእብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ እና ሁሉንም 24 መጽሐፍት እንዲሁም ሥርዓተ ነጥቦችን እና የአነባበብ ድምጾችን በሚያመለክት መልኩ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ በዕድሜ ከቀደሙ ወጥ ጥንታዊ መጻሕፍት መካከል የሚጠቀስ ነው።

መጽሐፍ ቅዱሱን አሜሪካዊው ጠበቃ እና የቀድሞ አምባሳደር አልፍሬድ ሞሰስ አስራኤል ውስጥ ለሚገኘው የአይሁድ ሕዝቦች ሙዚየም ብለው ነው የገዙት።

“ይህ የእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ ታላቅ ተጽእኖ ያለው እና ለምዕራባዊው ሥልጣኔ መሠረት ነው” ነው ሲሉ ሞሰስ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ጨምረውም “የአይሁድ ሕዝብ ንብረት በመሆኑ ደስ ብሎኛል። የመጽሐፉን ታላቅነት በመረዳት የዓለም ሕዝብ ሊያገኘው በሚችልበት ቦታ ላይ እንዲገኝ የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነበረ” ብለዋል።

መጽሐፍ ቅዱሱን ለመግዛት አሸናፊ የሆነው የጨረታ ገንዘብ በአውሮፓውያኑ 1994 ከዓለማችን ባለጸጎች መካከል አንዱ የሆነው የማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ፣ የሌዮናርዶ ዳ ቪንቺን ሳይንሳዊ የማስታወሻ ደብተር ለመግዛት የከፈለውን 30.8 ሚሊዮን ዶላርን የሚበልጥ ነው።

ነገር ግን በጨረታ ከተሸጡ ታሪካዊ ሰነዶች መካከል አንዱ የሆነው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያውን ዕትም ከሁለት ዓመት በፊት ከተሸጠበት ከ43.2 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።

ይህ “ዘ ኮዴክስ ሳሱን” በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስሙን ያገኘው ለንደን በሚገኘው ቤቱ በግለሰብ እጅ ያለ ትልቁ የእብራይስጥ መጽሐፍት ስብስብ ባለቤት ከሆነው ዴቪድ ሶሎሞን ሳሱን ነው።

ግለሰቡ መጽሐፍ ቅዱሱን በአውሮፓውያኑ 1929 የራሱ አድርጎት ቆይቷል።

በዚህ የእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት 24 መጽሕፍት የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ብሉይ ኪዳን ብለው የሚጠሩትን መጻሕፍትን አካቷል። ሌሎች ተመሳሳይ “አሌፖ ኮዴክ” የተባሉ መጽሕፍት ሶሪያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን በእሳት አደጋ ወድመዋል።

አሁን በከፍተኛ ገንዘብ የተሸጠው ቅዱስ መጽሐፍ ላይ በተደረገ ምርመራ እንደታወቀው የተዘጋጀው ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ሲሆን፣ የጎደሉት 12 ገጾች ብቻ እንደሆነ አጫራቹ ሶዝቢስ ገልጿል።

ለዘመናት ሲሸጋገሩ የነበሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መጽሐፉ ኻላፍ ቤን አብራሃም የተባለ ግለሰብ ለአይዛክ ቤን እስቂኤል አል-አታር የሸጠው ሲሆን፣ እሱም ኋላ ላይ ባለቤትነቱን ለሁለት ልጆቹ አሳልፎ ሰጥቶ ነበር።

መጽሐፉ ለበርካታ ዘመናት ከተደረጉ ጦርነቶች እና ውድመቶች በመትረፍ ለ500 ዓመታት ከታሪክ ተሰውሮ ቆይቶ እንደነበረ ይነገራል።

የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የቅርብ ጊዜ ባለቤት የነበረው የስዊዝ ኢንቨስተሩ ጃክ ሳፍራ ነበር። እሱም በአውሮፓውያኑ 1989 ለንደን ውስጥ በተካሄደ ጨረታ ላይ በ2.5 ሚሊዮን ዶላር ነበር የገዛው።