ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአፍንጫችን የሚወጣው ፈሳሽ ስለ ጤናችን ምን ይናገራል?
ከአፍንጫችን የሚወጣ ፈሳሽ ወይንም 'ንፍጥ' ራሳችንን ከበሽታ በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ያውቃሉ? ከዚህም በተጨማሪ ቀለሙ ብቻ በሰውነታችን ውስጥ ስላለው ነገር ለመረዳት እንደሚጠቅምስ?
በጥንታዊቷ ግሪክ ንፍጥ የሰውን ጤና እና ሰብዕና ለማመጣጠን ድርሻ ካላቸው አራት የሰውነት ፈሳሾች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
ሐኪሙ ሂፖክራቲስ አክታ፣ ደም፣ ቢጫ ሐሞት እና ጥቁር ሐሞት አራቱ "ሂውመረስ" የሚል ንድፈ ሃሳብ ፈጠረ።
አንድ ሰው እነዚህ ሂውመረስ ሚዛናቸውን ጠብቀው መገኘታቸው የስሜታችንን ሁኔታ ሊወስኑ ይችላሉ።
ከእነርሱ ውስጥ የአንዱ ከመጠን በላይ መጨመር በሽታን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ አክታ በአንጎል እና በሳንባ ውስጥ እንደሚፈጠር ይታሰብ ነበር። እና ቅዝቃዜ እና እርጥበት አዘል አየር ባለበት ወቅት ከመጠን በላይ ሊበዛ አልፎ ተርፎም የሚጥል በሽታ ሊያስከትል ይችላል።
እርግጥ ነው አሁን ከአፍንጫችን የሚወጣው ፈሳሽ የሰዎችን ሰብዕና እንደማይጎዳ ወይም በሽታን እንደማያመጣ እናውቃለን፤ይልቁንም እኛን ከበሽታ ለመከላከል ይጠቅመናል።
ማንም ሰው በማስነጠስ ወቅት በንፍጥ መዝረክረክን ወይም በአጠቃላይ ንፍጥን አይወድም።
በአፍንጫችን ውስጥ ያለው ንፍጥ ከሰው አካል ድንቅ ነገሮች መካከል አንዱ ነው ሊባል ይችላል።
የበሽታ መከላከል አቅማችንን አልፈው በመግባት ጤናችንን ከሚያቃውሱ ወራሪዎች ይጠብቀናል።
እና በውስጣችን ስላለው ነገር ጥልቅ ግንዛቤን የሚገልጽ ልዩ ውህድ አለው።
አሁን ሳይንቲስቶች ከኮቪድ-19 እስከ ሥር የሰደደ የሳንባ ሕመም ድረስ ያለውን ነገር በተሻለ ሁኔታ ለመመርመር እና ለማከም ንፍጥን በአግባቡ ለመመርመር ይሞክራሉ።
ይህ ለስላሳው እና በቀላሉ የሚጣበቀው ፈሳሽ የአፍንጫችን የውስጥ ክፍልን ከባክቴሪያ ይከላከላል። የአፍንጫችንን የውስጥ ክፍል ያጸዳል፤ ማንኛውንም ባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ የአበባ ብናኝ፣ ቆሻሻ፣አቧራ እና ሌሎች በሽታ አምጪዎች ወደ ሰውነታችን በመተንፈሻ አካሎቻችን በኩል ሊገቡ ይችላሉ።
ንፍጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ጥቃቅን በአፍንጫችን ውስጥ ባሉ ፀጉሮች በመታገዝ በውጪው ዓለም እና በውስጣችን መካከል መከላከያ ግንብ ሆኖ ያገለግላል።
በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን እና ክትባት ፕሮፌሰር የሆኑት ዳንዬላ ፌሬራ እንዳሉት የአዋቂ ሰው አካል በቀን ውስጥ ከ100 ሚሊ ሜትር በላይ ፈሳሽ ያመርታል። ነገር ግን ሕጻናት ከአዋቂዎች በበለጠ አፍንጫቸው ፈሻሽ ያመርታል።
የእኛ የንፍጥ ቀለም እና የፈሳሹ ወጥነት በሰውነታችን ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ በቀላሉ እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል።
ከአፍንጫችን ጥርት ያለ ፈሻሽ የሚወጣ ከሆነ እንደ የአበባ ዱቄት ወይም አቧራ የመሳሰሉ ረብሸውናል ማለት ነው።
ነጭ ንፍጥ ደግሞ ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ገብቷል ማለት ነው። ምክንያቱም ነጩ ፈሻሽ የሚፈጠረው ሰርጎ ገቦችን ለመዋጋት በተጠሩት ነጭ የደም ሴሎች አማካኝነት ነው። ንፋጥ ወደ ቢጫነት ሲቀየር ደግሞ የሞቱ ነጭ የደም ሴሎች በብዛት ተከማችተው እየወጡ ነው ማለት ነው።
የእርስዎ ንፍጥ ቀይ ወይም ሮዝ ከሆነ ደግሞ፣ ምናልባት አፍንጫዎትን በሚያጸዱበት ወቅት ውስጡን ጎድተውት ተቆጥቶ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ከአፍንጫ የሚወጣን ፈሻሽ ወይንም ንፍጥን መመልከት የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው።
በአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያን
አንጀታችን የተለያዩ ረቂቅ ተህዋሲያንን ይይዛል።ሰውነታችን የባክቴሪያዎች፣ የቫይረሶች፣ የፈንገሶች እና ሌሎች ረቂቅ ተሕዋስያን ሥነ ምኅዳር ነው ማለት እንችላለን።
በተመሳሳይም በንፍጣችን ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ረቂቅ ተህዋሲያን አስፈላጊ መሆናቸውን ሳይንቲስቶች ያምናሉ።
በእርግጥ ሳይንቲስቶች እነዚህ ረቂቅ ተህዋሲያን ከሰው ልጅ ጤና እና ከትክክለኛው የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት ጋር የተቆራኘ ነው ብለው ያምናሉ።
ሁሉም ሰው ንፍጥ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያን የተለያዩ ናቸው። በፆታችን፣ በዕድሜያችን፣ በምንኖርበት ቦታ፣ በአመጋገባችን እና የምናጨስ ከሆነ የተለያየ ይሆናል።
የረቂቅ ተህዋሲያኑ ስሪት ወደ ሰውነታችን በመተንፈሻ አካላችን በኩል የሚገቡ ወራሪዎችን ለመከላከል የሚረዳ ነው።
እነዚህ መስተጋብሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ደግሞ ስውር ናቸው። እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 የተደረገ ጥናት ለአብነት ያህል ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ስቴፕሎኮከስ (Staphylococcus ) የተሰኘ ባክቴሪያ በአፍንጫ ውስጥ በሕይወት የተገኘ ሲሆን ሰውን በመረረዝ፣ ትኩሳት እና መግል የተሞላ እብጠቶችን አስከትሏል።
ይህ ንፍጥ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲ እና ባክቴሪያ ምን ያህል አይረን አለው በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው።
ፌሬራ የጤናማ ንፍጥ ረቂቅ ተህዋሲያን ምን እንደሚመስሉ በትክክል ለማወቅ እየተመራመሩ ሲሆን፣ ይህንንም በየቀኑ በአፍንጫ ውስጥ የሚረጭ መድኃኒት ውስጥ በማካተት የንፍጥን ጤናን ለማጎልበት ያገለግላል።
ፌሬራ "አስቡት በአፍንጫችን ያለውን ነገር እዚያው የሚቆዩ እና የሚቆጣጠሩ ብዙ ጥሩ መልካም ዝርያዎችን ይዘን፣ መጥፎ ተህዋሲያን ገብተው እንድንታመም ብናደርግ" ሲሉ የሚያስቡትን ያስረዳሉ።
የፌሬራ ባልደረቦች በአፍንጫ ውስጥ የሚገኝ ትክክለኛው የረቂቅ ተህዋሲያን ዓይነቶች ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ለይተዋል።
እና እነዚህ ባክቴሪያዎች የሰዎችን የአየር መተላለፊያዎችን ተቆጣጥረው ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ እና ጤንነታቸውን ለማሻሻል ይችሉ እንደሆነ ለማየት እየሞከሩ ነው።
ፌሬራ እንደሚሉት ንፍጥ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያን ከበሽታ መከላከል ሥርዓት ጋር በጣም የተቆራኙ ስለሆኑ፣ በሽታ የመከላከል ሥርዓቱን እንዴት እንደሚያሳድጉ እና ክትባቶችን የበለጠ እንዲቀበሉ ለማድረግም እያጠኑት ነው።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ ሰው ለክትባት የሚሰጠው ምላሽ የሚወሰነው ባለው የረቂቅ ተህዋሲያን ዓይነት ነው።
ለምሳሌ በኮቪድ-19 ክትባት ላይ የተደረጉ ጥናቶች የንፍጥ ረቂቅ ተህዋሲያን ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ ይጠቁማሉ። እና በምላሹ ረቂቅ ተህዋሲያኑ ክትባቱ ውጤታማነት ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ፌሬራ "የኮቪድ-19 ክትባቶች እንዳንታመም ለመከላከል ጥሩ ነበሩ። ነገር ግን ቫይረሱን ማስተላለፋችንን ቀጠልን" ብለዋል።
"በእውነቱ በጣም የተሻሉ ክትባቶችን ቀጣዩ ትውልድ በኮቪድ-19ም ሆነ በጉንፋን ወይም ሌላ የመተንፈሻ አካል ቫይረስ እንዳይታመም የሚያደርግ መሥራት እንችል ነበር። ሁሉም ነገር በንፍጥ የበሽታ መከላከል ውስጥ ነው ያለው።"
ንቅለ ተከላ
የፌሬራ ምርምር ትክክለኛውን የንፍጥ ረቂቅ ተህዋሲያን ቀመር ለመጠቆም ሁለት ዓመታትን ሊወስድ ቢችልም በስዊድን ውስጥ ሳይንቲስቶች የጤናማ ሰዎችን ንፍጥ በራይኖሲነሲቲስ (rhinosinusitis) ምክንያት ለረጅም ጊዜ በተዘጋ አፍንጫ እና በአለርጂ ምክንያት የሚፈጠር ትኩሳት የሚታመሙ ሰዎች አፍንጫ ውስጥ በማስቀመጥ መፍትሄ ለማግኘት ቀደም ብለው ምርምር ጀምረዋል።
ተመራማሪዎቹ 22 ጎልማሶች በየቀኑ ከጤናማ ጓደኞቻቸው ወይም አጋሮቻቸው የተሰበሰቡ ንፍጦችን በሲሪንጅ ለአምስት ቀናት አፍንጫቸው ውስጥ እንዲጨምሩ ጠይቀዋል።
ቢያንስ በ16 ሕሙማን ላይ እንደ ሳል እና የፊት ሕመም ያሉ ምልክቶች እስከ ሦስት ወር ድረስ በ40 በመቶ ቀንሷል።
ጥናቱን የመሩት በስዊድን ሄልሲንግቦርግ ሆስፒታል የጭንቅላት እና የአንገት ቀዶ ጥገና አማካሪ አንደር ማርተንሰን "ይህ ለእኛ ታላቅ ዜና ነበር፣ ማንም አሉታዊ የጎንዮሽ ጉዳቶችን አላሳየም" ብለዋል።
እነዚህ ሙከራዎች በሌሎች ላቦራቶሪዎች ውስጥ በአንጀት ረቂቅ ተህዋሲያን እና የዓይነ ምድር ንቅለ ተከላ ላይ የተሠራ ጥናትን እንደመነሻ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
ያ የመጀመሪያው የሙከራ ምርምር የእነዚህ ሰዎች ንፍጥ ረቂቅ ተህዋሲያን እንዴት እንደተቀየሩ እና በአፍንጫቸው ውስጥ ባሉ ተህዋሲያን ላይ ምን እንደተፈጠረ፣ እንደጨመሩ ወይም እንደሚቀነሱ የሚያሳዩ መረጃዎች አልሰበሰበም።
ስለዚህ ሌላ ትልቅ እና ትኩረት ያደረገ ሙከራ በመካሄድ ላይ ነው።
በእርግጥ ንፍጥ ሥር ለሰደደ የአፍንጫ እና የሳንባ በሽታዎች ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።
በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የአንገት በላይ ስፔሻሊስት የሆኑት ጄኔፈር ሙሊጋን የዓለምን ሕዝብ ከ5 እስከ 12 በመቶ የሚያጠቃው ሥር የሰደደ የራይኖሲኑሲቲስ (rhinosinusitis) እና የአፍንጫ ውስጥ እብጠት (nasal polyps) ያለባቸውን ሰዎች ለማጥናት ንፍጥን ይጠቀማሉ።
በሥራዋ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የአፍንጫ ኅብረ ሕዋሳት ከራይኖሲኑሲቲስ ሕሙማን በቀዶ ሕክምና ታስወግድ ነበር።
ነገር ግን ይህ የሕክምና ዓይነት ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አላገኘችውም። የእርሷ ጥናት እንደሚያሳየው ንፍጥ አንድ ሰው በራይኖሲኑሲቲስ ሲያዝ በሰውነቱ ውስጥ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ በቅርበት ለመመርመር ትክክለኛ አማራጭ ሊሆን ይችላል።
"እኛ እዚህ ያሉ ወንጀለኞች እነማን እንደሆኑ ለማቃለል እየተጠቀምን ነው፣ ይህን ሁኔታ ማን እየነዳው ነው?" ይላል ሙሊጋን እያንዳንዱ በሽተኛ ለራይኖሲኑሲቲስ መንስኤው ትንሽ የተለየ መገለጫ አለው ሲል ተናግሯል።
በተመሳሳይ፣ ከዚህ በፊት የሚደረግ ሕክምና በአብዛኛው እንደ ሙከራ ነበር፤ ከታካሚ ታካሚ በጣም የተለያየ እና አንዳንዴም በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር የሚፈጅ እና ወራትን ይወስድ ነበር።
ሙሊጋን ንፍጥን በመመርመር በፍጥነት አስፈላጊውን ሕክምና ወይም ቀዶ ሕክምና ለመለየት ይረዳል ትላለች።
በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ምሁራን የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ንፍጥን በመመርመር የረቂቅ ተህዋሲያንን ናሙና ለመለየት የሚያገለግል መሳሪያ ሠርተው የፈጠራ ባለቤትነት ለማግኘት እየጠበቁ ነው።
በ2025 የምግብ እና መድኃኒቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ከአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያንን ለመመርመር የሚያገለግለውን መሳሪያ አጽድቋል።
መሳሪያው ከአፍንጫ ፈሳሽ በመውሰድ ናሙናዎችን በመሰብሰብ በውስጡ የሚገኙ ረቂቅ ተህዋሲያንን ይለያል፤ ይህም ናሙና አወሳሰድ ወጥነት እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ሳይሆን የምርምሮች መለያየትን ይቀንሳል።
ሙሊጋን ሰዎች የማሽተት ስሜታቸውን እንዲያጡ የሚያደርጋቸውን ነገር ለማጥናት ተመሳሳይ መሳሪያዎችን ተጠቅማለች።
ቡድኗ ቀድሞውንም ቢሆን አፍንጫ ላይ የሚረጭ ቫይታሚን ዲ በሲጋራ ምክንያት በተከሰተ እብጠት ምክንያት የማሽተት አቅማቸውን ያጡ ሰዎችን ለማከም የሚረዳ መድኃኒት አግኝቷል።
ስለዚህ እነዚህ የመመርመሪያ መሳሪያዎች እና ሕክምናዎች ለሳንባ በሽታዎችም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አይኤል-26 ፕሮቲን በሕሙማን ንፍጥ ውስጥ የሚገኙበትን መጠን በቀላሉ በመመርመር አንድ ሰው ለከባድ የሳንባ ምች በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸውን ማወቅ ይችላሉ።
ይህ በአጫሽ ሰዎች ዘንድ የሚከሰት በሽታ ሲሆን፣ በዓለም ላይ አራተኛው በጣም የተስፋፋ የሞት መንስኤ ነው። ንፍጥን በመመርመር እና ያለውን ረቂቅ ተህዋሲያን በማየት ሕመሙን ቀድሞ ማወቅ እና በፍጥነት ማከም ይቻላል።
በተመሳሳይ ዘዴ በዓለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎች በተመሳሳይ ዘዴ አስምን፣ የሳንባ ካንሰርን፣ አልዛይመርን እና ፓርኪንሰንን ለመለየት እየሞከሩ ነው።
ሙሊጋን "ንፍጥ በግል የተዘጋጀ የወደፊቱ መድኃኒት ነው ብዬ እኔ በሙሉ ልቤ አምናለሁ" ብላለች።