እስራኤል ለ60 ቀናት በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን ትራምፕ አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ "አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን" ለማሟላት ተስማምታለች ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዚደንቱ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ እንደጻፉት ከሆነ በምክረ ሃሳቡ ስምምነት ወቅት "ጦርነቱን ለማቆም ከሁሉም አካላት ጋር እንሰራለን" ያሉ ሲሆን ቅድመ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

"ሰላም ለማምጣት በጣም ጠንክረው የሠሩት ኳታራውያን እና ግብፃውያን የመጨረሻውን ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ። . . . ሃማስ ይህንን ስምምነት ይቀበላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም የተሻለ አይሆንም፤ እየባሰ ነው የሚሄደው" ሲሉ ትራምፕ ጽፈዋል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቀቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻዋን ጀምራለች።

በግዛቱ በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 56,647 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ይቀበል አይቀበል ወዲያውኑ አላሳወቀም።

የትራምፕ መልዕክት የተሰማው በሚቀጥለው ሳምንት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በፊት ነው።

ፕሬዚዳንቱ የሁለቱን ውይይትት "በጣም ጠንከር" ያለ እንደሚሆን ገልቨዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ኔታንያሁ በጋዛ ያለውን ጦርነት ማቆም ይፈልጋሉ ብለው ያምናሉ።

ትራምፕ አክለውም " ይፈልጋል። እንደሚፈልግ ልነግራችሁ እችላለሁ። በሚቀጥለው ሳምንት ስምምነት ላይ የምደርስ ይመስለኛል።"

ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮን ዴርመር፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በዋሽንግተን ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል "ፍፁም" የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ትፈልጋለች፤ ነገር ግን ሐማስ "የሚያመቻችም አልሆነም" ብለዋል።

"በሐማስ ላይ ጫና እየፈጠርን ነው። ወደ ድርድር ጠረጴዛው ካልመጡ ታጋቾቹን ለመመለስ ያለን ብቸኛው አማራጭ ተጨማሪ ወታደራዊ ጫና መፍጠር ብቻ ነው" ሲሉ ዳኖን ተናግረዋል።

አክለውም "ጦርነቱ የሚቆመው ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ነው" ብለዋል።

ወደ 50 የሚጠጉ የእስራኤል ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።

ባለፈው ሳምንት አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለስልጣን ለቢቢሲ አደራዳሪዎች በጋዛ አዲስ የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነትን እንዲደረስ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው ነገርግን ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር ቆሟል ብለው ነበር።

እስራኤል ግጭቱ ሊቆም የሚችለው ሐማስ ሙሉ በሙሉ ሲፈርስ ነው ስትል ተናግራለች። ሐማስ ዘላቂ ስምምነት ላይ እንዲደረስ እና እስራኤል ሙሉ በሙሉ ከጋዛ እንድትወጣ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል።

የትራምፕ መልዕክት የመጣው እስራኤል በሰሜን ጋዛ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷን አጠናክራ ከመቀጠሏ በፊት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ከሰጠች በኋላ ነው ።

እስራኤል በጋዛ ከተማ በባህር ዳርቻ በሚገኝ ካፌ ላይ ሰኞ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 20 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የሕክምና ባለሙያዎችና የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦር በዚህ ሳምንት በጋዛ ውስጥ በአሜሪካ እና በእስራኤል በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ወደሚተዳደሩ የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከላት ሲቃረቡ "የተጎዱ" ሰላማዊ ዜጎች በሚመለከት የወጡ ሪፖርቶችን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

ከ170 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አወዛጋቢው ይህን የእርዳታ ድርጅት እንዲዘጋ ጠይቀዋል።

እንደ ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረን ያሉ ድርጅቶች የእስራኤል ጦር ዕርዳታ በሚሹ ፍልስጤማውያን ላይ "በተደጋጋሚ" ተኩስ ይከፍታል ብለዋል።

እስራኤል ይህንን ውንጀላ በመቃወም ድርጅቱ ሐማስን የእርዳታ ስርጭት ላይ ያለውን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት አስፈላጊ ነው ስትል ተናግራለች።

በመጋቢት ወር እስራኤል በጋዛ ላይ አዲስ ጥቃት ስትሰነዝር ከዚህ ቀደም ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሷል።

የእስራኤል ጦር ድርጊቱን "ሐማስ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም፣ ኃይልን ማሰባሰብ እና እንደገና ለማስታጠቅ ያለውን ዝግጁነት መሰረት በማድረግ የተደረገ ቅድመ ድብደባ ነው" ሲል ገልጿል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥር 19 የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት እርከኖች እንዲኖሩትሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ ግን ማለፍ አልቻለም።

በዚህ ስምምነት መሠረት ሁለተኛው ደረጃ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ ፣ በእስራኤል ውስጥ ለታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ ታግተው የነበሩትን መልቀቅ እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን ያካትት ነበር።