የሲሪላንካው ፕሬዝደንት በጦር አውሮፕላን ከአገር ሸሹ

የስሪ ላንካ ፕሬዝደንት ጎታባያ ራጃፓክሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የስሪ ላንካ ፕሬዝደንት ጎታባያ ራጃፓክሳ

ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን ተከትሎ ሕዝባዊ አመጽ በርትቶባቸው የነበሩት የሲሪላንካው ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ በጦር አውሮፕላን ከአገር መሸሻቸው ተዘገበ።

የ73 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ከባለቤታቸው እና ከሁለት የደኅንነት አባላት ጋር ወደ ማልዲቭስ ደሴት ማቅናታቸውን የአገሪቱ አየር ኃይል አስታውቋል።

ፕሬዝዳንቱ ማልዲቭስ መዲና መድረሳቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል። ፕሬዝዳንቱ በማልዲቭስ እንደማይቆዩ እና ወደ ሦስተኛ አገር እንደሚሸጋገሩም ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ አገር ጥለው መሸሻቸው ለበርካታ አስርት ዓመታት በአንድ ቤተሰብ አባላት ተይዞ የነበረውን ሥልጣን እንዲያበቃ ያደርገዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ተቃዋሚዎች መኖሪያ ቤታቸውን በኃይል ጥሰው ከገቡ በኋላ ፕሬዝዳንቱ አድራሻው ባልተገለጸ ቦታ ተሸሽገው ቆይተው ነበር።

ፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ አገር ጥለው መሸሻቸውን ይፋ ከተደረገ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሪላንካውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

ሲሪላንካ ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ በፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል።

ከቀናት በፊት ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች ወደ ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት በኃይል ጥሰው ከገቡ በኋላ ፕሬዝደንቱ ሥልጣን እስኪለቁ ከመኖሪያ ቤቱ አንወጣም ብለው ነበር።

ተቃዋሚዎቹ ወደ ወደ ቤተ መንግሥቱ ከገቡ በኋላ፤ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሲዋኙ እና በፕሬዝዳንቱ አልጋ ላይ ተኝተው ታይተዋል። በመኖሪያ ቤቱ ላይም ጉዳት እንደደረሰ ተነግሯል።

ሲሪላንካ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን የጨረሰች ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟታል። እንደ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ምግብ የመሳሰሉ መሠረታዊ ቁሶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ተስኗታል። 

ሲሪላንካውያን ለዚህ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፕሬዝዳንት ራጃፓክሳን እና አስተዳደራቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከቀናት በፊት ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ያመለከቱ ቢሆንም፤ አዲስ በሚመጣ መንግሥት ለእስር እንዳይዳረጉ በመስጋት ከአገር መውጣትን ስለመምረጣቸው መላ ምቶች እየተሰጡ ነው።