ለትግራይ መልሶ ግንባታ የሚውል ስምምነት መፈረሙን መንግሥት አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት በቀረው ጦርነት የተጎዳችውን ትግራይን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍን ለማግኘት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ስምምነት ደረሰ።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው፣ ይህ ፕሮጀክት በጦርነቱ የተጎዱትን የአገሪቱን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ከተያዙት አገር አቀፍ ዕቅዶት መካከል አንዱ እንደሆነና በዓለም ባንክ እንደሚፈደገፍ አመልክቷል።
ይህ በዓለም ባንክ ድጋፍ የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት የተያዘው ፕሮግራምን በተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት የፕሮጀክቶች አገልግሎት ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ የገንዘብ ሚንስቴር መካከል ነው ስምምነት የተፈረመው።
በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘጋጀው ይህ ዕቅድ በትግራይ ክልል በጦርነቱ የወደሙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት እና ለወሲብ ጥቃት የተለያዩ አገልግሎቶችን ማቅረብ ነው።
በተፈረመው ስምምነት መሰረት የመንግሥታቱ ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት “በትግራይ ያለው ሁኔታ አስኪሻሻል ድረስ ባለው መዋቅር አማካይነት ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል” ብሏል።
በተጨማሪም ፆታዊ ጥቃት ላጋጠማቸው ሰዎች የሚደረገው ድጋፍ በሌላ ሦስተኛ ወገን በኩል ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
ይህንን ስምምነት በተመለከተ የትግራይ ኃይሎች አስካሁን በይፋ ሰጡት ምላሽ የለም።
ነገር ግን የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ስምምነቱን የተመለከተው ዜና ይፋ መሆኑን ተከትሎ በትዊተር ላይ እንደጻፉት፣ ተደረሰ የተባለውን ስምምነት እንዳልተረዱትና እንዴት እንደሚሰራ በመጠየቅ ምላሽ እንደሚጠብቁ አስፍረዋል።
ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ ለወራት ተቋርጦ የነበረው የእርዳታ አቅርቦት መልሶ ከመጀመሩ ውጪ በመንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ይህ ነው የሚባል ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት አልተደረሰም።
በተጨማሪም በተግራይ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ እና የቴሌኮም አገልግሎቶች በሌሉበት ሁኔታ ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ስለሚሆንበት መንገድ የተባለ ነገር የለም።
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች የተዛመተው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ካስከተለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ ትልቅ ውድመትን አስከትሏል።
የፌደራል መንግሥት እና የመንግሥታቱ ድርጅት ፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸው፣ ባለፉት በርካታ ወራት በትግራይ ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ሥራ ይመለሱ እንደሆነ የተባለ ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በመንግሥትና በተባበሩት መንግሥታት የፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት መካከል ለተደረሰው ስምምነት ማስፈጸሚያ በዓለም ባንክ በኩል 300 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተነግሯል።
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ከዋነኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ይህን አይነት ድጋፍ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲለቀቅ ይህ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በኢትዮጵያ የብድር ሁኔታ ላይ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም. እንደሚመክር ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ይህ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ብድሯን የምትከፍልበትን ጊዜ ለማሸጋሸግ እንዲቻል ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።
በፈረንሳይ እና በቻይና የሚመራው ኮሚቴ መስከረም 2013 ዓ.ም. ላይ በዚሁ ጉዳይ ላይ መክሮ የነበረ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ለአገሪቱ አዎንታዊ ምላሽ ሳያስገኝ ቀርቶ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ አመራሮች ጦርነቱን ለማብቃት የሚያስችል ድርድር ለማድረግ ፈቃደኞች መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ አስካሁን የተጀመረ ተጨባጭ እርምጃ የለም።












