ኦሪገን ከወታደሮች ስምሪት ዕቅድ ጋር ተያይዞ የትራምፕ አስተዳደርን ከሰሰች

የኦሪገን ግዛት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ዘብ አባላትን በፖርትላንድ እንዲሰማሩ መወሰናቸውን ተከትሎ "ሕገወጥ" ነው በማለት ክስ መሰረተች።

የአሜሪካውን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ትዕዛዝ ተከትሎ የብሔራዊ ዘብ አባላት ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት በኦሪገን ግዛት በምትገኘው ፖርትላንድ ከተማ ይሰማራሉ።

እሁድ ዕለት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የላኩት ደብዳቤ፣ተቃውሞዎች በሚካሄዱባት አሊያም ይካሄድባታል ተብሎ በሚታሰበው ፖርትላንድ ከተማ የፌደራል ንብረቶችን ለመጠበቅ ሲባል ቢያንስ 200 የብሔራዊ ዘብ አባላት እንደሚሰማሩ ገልጿል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት የኢሚግሬሽን ማዕከላትን ኢላማ የሚያደርጉ ተቃዋሚዎችን ለማስቆም በከተማዋ የሚሰማሩት ወታደሮች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም "ሙሉ ኃይላቸውን" እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል።

ኦሪገን በበኩሏ የብሔራዊ ዘብ አባላትን በፖርትላንድ ማሰማራት "ሕገወጥ" ነው ስትል የትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ በመመስረት ምላሽ ሰጥታለች።

እሁድ ዕለት በኦሪገን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዳን ሬይፊልድ የቀረበው የክስ መዝገብ፣ የፕሬዚደንቱን እርምጃ "ግጭት ቀስቃሽ እና ሕጋዊ መሠረት የሌለው" ያለው ሲሆን የሕዝብ ቁጣ በመቀስቀስ የማኅበረሰቡን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ገልጿል።

የትራምፕ አስተዳዳር ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል ጥብቅ እርምጃ እየወሰዱ ባሉበት ወቅት በአሜሪካ ከተሞች ተጨማሪ የወታደሮች ስምሪት መስፋፋት እየታየ ነው።

ትራምፕ ውሳኔው በከተማዋ በከበባ ውስጥ የሚገኙትን የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ መሠረተ ልማቶችን በአንቲፋ እና በሌሎች የአገር ውስጥ የሽብር ድርጅቶች ከሚፈፀምባቸው ጥቃት ለመከላከል እንደሚረዳ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ሆኖም ዲሞክራት ሕግ አውጭዎች እርምጃውን የተቃወሙት ሲሆን ትራምፕ በፖርትላንድ የፌደራል ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው ያሉትን ሃሳብ አልተቀበሉትም።

የኦሪገን ገዥ ቲና ኮቴክም ቅዳሜ እለት " በፖርትላንድ ምንም ዓይነት ብሔራዊ ስጋት የለም። ማኅበረሰባችን ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ ነው" ብለዋል።

በፖርትላንድ የሚገኘው የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተቋማት ከሰኔ ወር ጀምሮ በተቃዋሚዎች ዒላማ የሆኑ ሲሆን ተቃውሞው ወደ ግጭት አምርቶ ጉዳት ያስከተለበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

ከአውሮፓውያኑ መስከረም 8 ጀምሮም የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ በ26 ግለሰቦች ላይ በፖሊስ መኮንኖች ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ላለመዋል በመታገል እና እሳት በማስነሳት የፌደራል ክስ መስርቷል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አርብ ዕለት እንደገለጸውም ተቃዋሚዎች በፖርትላንድ በሚገኘው እና የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቋም ላይ በተደጋጋሚ ጥቃትና ከበባ ፈፅመዋል።

በዚህም በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና የፌደራል ሕግን በመጣስ ክስ እንደተመሰረተባቸው መሥሪያ ቤቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ገልጿል።

"በቅርቡ የአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ የተፈረጀው ሮስ ሲቲ አንቲፋ በሕገ ወጥ መንገድ የስደተኛ ማዕከል መኮንኖች ላይ ድብደባ ፈፅሟል" ብሏል።

" የመኖሪያ ቤታቸውን አድራሻ በበይነ መረብ እና በበራሪ ወረቀቶች ላይ አትመዋል። ከአንቲፋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችም በአገር ውስጥ ደኅንነት ሰራተኞች ላይ የግድያ ማስፈራሪያ ልከዋል" ሲል የአገር ውስጥ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም አንቲፋ የተባለው ቡድን የአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ እንዲፈረጅ ትራምፕ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

'አንታይ ፋሺስት' [ፀረ ፋሽስት] - አንቲፋ በዋናነት በግራ አክራሪ አቀንቃኞች የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን በአሜሪካ ማንኛውም ቡድን በአገር ውስጥ የሽብር ድርጅት ሆኖ እንዲቋቋም የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕጋዊ መንገድ የለም።

በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ፍረጃዎች የመናገር ነጻነትን እና የመሰብሰብ መብትን በሚጠብቀው ሕግ መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

ዴሞክራት ሕግ አውጭዎች የፕሬዚደንቱን ትዕዛዝ እና በኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ወኪሎች ላይ ተፈፅሟል የተባለውን ድርጊት ኮንነዋል።

የኦሪገን ሴናተር ሮን ዋይድን አርብ ዕለት ሲናገሩ የፌደራል ኃይሎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ በሞተው - ጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የፌደራል ፖሊሶች መሰማራታቸውን በማስታወስ የፌደራል ወኪሎች ከአምስት ዓመት በፊት የፈፀሙትን ጨዋታ እንደገና ሊመልሱት እንደሚችሉ የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች አሉን ብለዋል።

በመሆኑም " የኦሪገን ነዋሪዎች ትራምፕ ግጭት ለመቀስቀስ በዘረጉት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ እናስጠነቅቃለን" ብለዋል ሴናተሩ።

የአካባቢው ሕግ አውጭዎች ለማኅበረሰቡ አስጊ ያልሆኑ ሰዎችን በማሳደድ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ከስሰዋል።

"ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ኢላማ የሚያደርገው ወንጀል የሰሩ ሰዎችን ለማሰር እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነው ብሏል።ይህንን ነው የነገሩን ፤ ነገር ግን እየተመለከትን ያለነው ይህንን አይደለም" ብለዋል የዴሞክራት ተወካይ የሆኑት ሱዛን ቦናሚሲ።

ለዚህም በልጁ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የታሰረውን አባትን እና በኦሊምፒክ ብሔራዊ ደን የተነሳውን እሳት እየተጋፈጠ ባለበት የታሰረውን የእሳት አደጋ ሰራተኛን ጨምሮ በቅርቡ የተፈፀመ ክስተትን በዋቢነት አንስተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን በሚገኘው ካቶ ተቋም የታተመውን መረጃ ጠቅሰዋል።መረጃው በኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ከታሰሩት መካከል 65 በመቶ የሚሆኑ ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ እንዳልቀረበባቸው የሚያስረዳ ነው።

እርምጃው ምንም እንኳን በዴሞክራቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም በአንዳንድ የሪፐብሊካን ባለሥልጣናት ድጋፍ አግኝቷል።

የአሜሪካ የሰራተኛ ሚኒስትር ሎሪ ቻቬዝ ዲሪመር ሕገ ወጥነት ፖርትላንድን ወደ የወንጀል መናሃሪያነት እንደቀየራት መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የኦሪገን የሪፐብሊካን ተወካይ ሆነው ያገለገሉት ቻቬዝ ትራምፕ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቋማትን ለመጠበቅ እና አሜሪካን ታላቅ ለማድረግ እርምጃ እየወሰዱ በመሆናቸው አመስግነዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ በሎስ አንጀለስ እና ዋሽንግተን ዲሲ የብሔራዊ ዘብ አባላትን አሰማርተዋል።በሚቀጥለው ሳምንትም የፌደራል ወኪሎች በቴኒስ ሜምፒስ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል።

በሎስ አንጀለስ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለመያዝ በሚደረገው ሒደት የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመቆጣጠር 2ሺህ የፌደራል ወታደሮች እንዲሰማሩ ፕሬዚደንቱ አዘዋል።ለበርካታ ቀናትም ግጭቶች ተቀስቅሰው የነበረ ሲሆን ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ጥቅም ላይ ውሏል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በካሊፎርኒያ የሚገኙ የፌደራል ዳኛ በሎስ አንጀለስ የተደረገው የብሔራ ዘብ አባላት ስምሪት ሕገ ወጥ ነው ያሉ ሲሆን ለአገር ውስጥ ጉዳይ የጦር ኃይልን መጠቀምን በተመለከተ የፌደራል መንግሥት ያለውን ሥልጣን የሚወስነውን ሕግ የሚጥስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም ፕሬዚደንቱ በኦሪገን የፌደራል ኃይሎችን ለማሰማራት ሕጋዊ መሠረት ይኑራቸው አይኑራቸው ግልጽ አይደለም።