የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ወቅት ያወለቁት የእጅ ሰዓት እያነጋገረ ነው

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ መሀል የእጅ ሰዓታቸውን ማውለቃቸው እያነጋገረ ነው።

ፕሬዝዳንት ማክሮን በቀጥታ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ የቀረቡት ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የጡረታ ዘመን ዕድሜን በተመለከተ ለማብራራት ነበር።

ሆኖም ድንገት የእጅ ሰዓታቸውን ደበቅ አድርገው ማውለቃቸው በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ትልቅ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

የርሳቸው ተቺዎች እንደሚሉት ማክሮን ችግርና ድህነት የሚያውቁ መሪ አይደሉም።

የፈረንሳይ ሕዝብ በቁጣ ገንፍሎ አደባባይ ወጥቶ ሳለ እርሳቸው ግን ይህ ግድ አልሰጣቸውም፤ አይሰጣቸውምም ሲሉ ተቃዋሚዎች ይተቿቸዋል።

ማክሮን የፈረንሳይ ሃብታሞች ፕሬዝዳንት እንጂ ድሀውን አይወክሉም ይላሉ ተቃዋሚዎች፣ በተደጋጋሚ።

የዚህ አንዱ ማሳያ አድርገው የሚያነሱት ደግሞ ማክሮን በቃለ ምልልስ ወቅት ከተመሳሳይ ወቀሳ ለማምለጥ በሚል “ቅንጡ” የተባለ የእጅ ሰዓታቸውን ማውለቃቸው ነው ይላሉ እነዚህ ተቺዎቻቸው።

የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ቃለ አቀባይ ግን ፕሬዝዳንት ማክሮን ሰዓቱን ያወለቁት ከጠረጴዛ ጋር እየተነካካ ድምጽ እየፈጠረ ስላስቸገረ ነው ሲል አስተባብሏል።

በፈረንሳይ የጡረታ ዘመን ዕድሜ ከ62 ወደ 64 ከፍ እንዲል በማክሮን መንግሥት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ በዚያች አገር ከፍተኛ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ከራርሟል።

ይሁንና የማክሮን አስተዳደር የሕዝብን ተቃውሞ ከቁብ የቆጠረ በማይመስል ሁኔታ ዕቅዱን ገፍቶበታል።

ማክሮንን ‘የሃብታሞች ብቻ ፕሬዝዳንት’ እያሉ የሚተቹት ተቃዋሚዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ወቅት ማክሮን ያወለቁት ሰዓት እስከ 80ሺህ ዩሮ እንደሚወጣ ይሞግታሉ።

ይህ የሆነው ባለፈው ረቡዕ በነበረ ቃለ ምልልስ ሲሆን ማክሮን ሁኔታዎችን ለማስረዳት እጃቸውን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት ድምጽ ይፈጠር ነበር።

በዚህ የተነሳ ማክሮን የእጅ ሰዓቱን ከጠረጴዛ ሥር ሸሸግ አድርገው አውልቀውታል።

ያቺ ሰዓታቸውን ያወለቁበት ቅጽበት በቃለ ምልልሱ በካሜራ አለመያዟ ጉዳዩን ለተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ መላምቶች ክፍት እንዲሆን አድርጓል።

አንድ የግራ ዘመም ፓርቲ እንደራሴ በትዊተር ሰሌዳቸው “ማክሮን ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋዮች እንኳ መሠረታዊ ፍጆታዎችን የመግዛት አቅማቸው ጨምሯል ሲል ይከራከራል፤ ይህን ለማስረዳት ግን ቅንጡ ሰዓቱን ማውለቅ ነበረበት።” ሲሉ ተሳልቀዋል።

ማክሮን ያወለቁት ሰዓት በእርግጥ ዋጋው ስንት ነው የሚለው ብዙ ያነጋገረ ሲሆን እስከ 80ሺህ ፓውንድ የገመቱት አሉ።

የኤሊዜ ቤተመንግሥት ቃል አቀባዮች ግን ለፈረንሳይ ሚዲያ እንደተናገሩት ሰዓቱ “ቤል ኤንድ ሮስ ቪ-92” ሞዴል እንደሆነ አስረድተዋል።

የእጅ ሰዓቱ የኤሊዜ ቤተመንግሥት እንዳለው ከሆነ በድረ ገጽ መሸጫ ዋጋው ከ3ሺህ ፓውንድ እንደማይበልጥ ያሳያል።

ኤሊዜ ቤተመንግሥት ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንቱ የእጅ ሰዓቱን አዘውትረው እንደሚያስሩትም አብራርቷል።

ማክሮን ለዓመታት ‘ከድሃው ፈረንሳዊ ልቡ የራቀ መሪ’ እየተባሉ ይተቻሉ።

የሃብታሞች ፕሬዝዳንት እያሉ የሚጠሯቸውም አሉ።

ባለፈው የካቲት አገሪቱ በተቃውሞ እየተናጠች ማክሮን ቢሊየነሩን የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስን የፈረንሳይን ትልቁን የክብር ኒሻን መሸለማቸው ብዙዎቸን አበሳጭቶ ነበር።

ማክሮንን አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸውን የጡረታ ዕድሜን ማራዘም ጉዳይ በፓርላማ ድምጽ ሳይሰጥበት ልዩ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅመው ነው ተግባራዊ እንዲሆን ያዘዙት።

ይህን ያደረጉት ድምጽ ከተሰጠበት ውድቅ ሊደረግ ይችላል ከሚል ስጋት ነው።

ይህን ተከትሎ አሁንም በፈረንሳይ የአደባባይ ተቃውሞና የሥራ ማቆም አድማዎች እየተደረጉ ነው።

በዚህ የተነሳ የንጉሥ ቻርለሥ ሣልሳዊ ወደ ፈረንሳይ ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።