አሜሪካ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሰኔ ወር እንዲያበቃ እንደምትፈልግ ዜሌንስኪ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service of Ukraine
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገች ያለችው ጦርነት ሰኔ ወር ላይ እንዲያበቃ አሜሪካ እንደምትፈልግ ተናገሩ። ሁለቱ ወገኖች በሚቀጥለው ሳምንት በአሜሪካ ለሚካሄደው ንግግር መጋበዛቸውንም ዜሌንስኪ ገልጸዋል።
" አሜሪካ ሁለቱን ተደራዳሪ ቡድኖች - ሩሲያ እና ዩክሬንን በሳምንት ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ ምናልባትም በሚያሚ እንዲገናኙ ሃሳብ ስታቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በእኛ በኩል በንግግሩ ላይ እንደምንሳተፍ አረጋግጠናል።" ብለዋል።
ድርድሩን በተመለከተ ከዋሽንግተንም ሆነ ከሞስኮ ወዲያውኑ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ግጭቱ እንዲያበቃ ግፊት እያደረጉ ነው።
በአሜሪካ አደራዳሪነት በአቡዳቢ የተካሄደው ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግርም አርብ ዕለት ተጠናቋል።
የድርድሩ ውጤት እና ሒደት ባይገለጽም፤ ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች በተናገሩበት ወቅት " ዩክሬን እንድትስማማ ግፊት እየተደረገባት ያለውን የግዛት ጉዳይን ጨምሮ "አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሆነው ቀርተዋል" ብለዋል።
ተደራዳሪ አካላቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ላይ መወያየታቸውን የገለጹት ዜሌንስኪ፣ በተወካዮች አማካኝነት ሳይሆን በመሪዎች መካካል የሦስትዮሽ ንግግር ሊደረግበት የሚችልበት ሁኔታም ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም "ለዚህ ለመዘጋጀት አስፈላጊ ነገሮች አሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ስምምነቱ ላይ ለመድረስ የተሰጣቸው ቀነ ገደብ እንደነበር የተጠየቁት ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ "አሜሪካኖቹ ሁሉም ነገር ሰኔ ወር ላይ እንዲጠናቀቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል" ብለዋል።
ይህንን ከበጋ በፊት ማድረግ የፈለጉበት ምክንያትም በአሜሪካ ያለው የአገር ውስጥ ጉዳይ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል እንደሆነ ተረድተናል ብለዋል። ይህም በአሜሪካ መንግሥት የኃይል ሚዛን ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ የሚችለውና ኅዳር ወር ላይ የሚካሄደው ማሟያ ምርጫን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም ሩሲያ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት መቀጠሏን የዩክሬን የኢነርጅ ሚኒስትር ደኒይስ ሽምይሃል በቴሌግራም ገፃቸው ላይ ጽፈዋል።
አርብ ዕለት ምሽት በተፈፀመው ጥቃት ብቻ ከ400 በላይ ድሮኖች እና 40 ሚሳኤሎች መሳተፋቸውን ዘሌንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ገልጸዋል።
ሆኖም አብዛኞቹን በአየር መከላከያ ሥርዓታቸው ቢከሽፉም ሁሉም አለመሆናቸውን የዩክሬን ጦር አስታውቋል። የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማዎች የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች እንደሆኑም ጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት በምዕራብ የአገሪቷ ግዛት ልቪቭ የሚገኝ የኃይል ማመንጫ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት እንደተቋረጠባቸው የክልሉ ኃላፊ ማክስይም ኮዢትስከይ ገልጸዋል።
በያሆቲን በተፈፀመ የድሮን ጥቃትም በአንድ መጋዘን ሕንጻ ላይ እሳት ማስነሳቱን የዩክሬን የድንገተኛ አገልግሎት አስታውቋል።
ዩክሬንም በሩሲያ ላይ ጥቃት የፈፀመች ሲሆን በምዕራባዊ ትቬር ክልል የሚገኘውን የሚሳኤል ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ መምታቷን የዩክሬንን የደኅንነት ባለሥልጣናትን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በደቡባዊ ሳራቶቭ ክልልም የነዳጅ ዘይት ማከማቻ መምታቷን ዩክሬን ገልጻለች። ሩሲያ ግን አዲስ የተፈፀሙትን ጥቃቶች በተመለከተ ያለችው ነገር የለም።
ሞስኮ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ባለው ቅዝቃዜ ምክንያት ጥቃት እንዲያቆሙ ቭላድሚር ፑቲንን ከጠየቁ በኋላ ሩሲያ አቁማው የነበረውን ጥቃት ሰኞ ዕለት እንደ አዲስ ጀምራለች።
ትራምፕ ሩሲያ ጥቃቱን እንድታቆም የተሰጣት ጊዜ እሁድ ዕለት ተጠናቋል ብለዋል። ኪየቭ ግን በጊዜ ሰሌዳው ላይ ቅሬታ አንስታለች።
ሩሲያ በበኩሏ "ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማምጣት ቁርጠኛ አይደለችም" ስትል ዩክሬንን ከሳለች።
አርብ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌቭ ላቭሮቭ ዩክሬን በሩሲያ ጦር ከፍተኛ ጀነራል ላይ በመተኮስ ዩክሬንን ወንጅለዋል። ይህም ድርድሩን ለማደናቀፍ ያለመ ነው ብለዋል።
ከተኩሱ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ ግን አልታወቀም።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከከፈተች ጀምሮ 55 ሺህ የሚሆኑ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስታውቀዋል።
ቢቢሲ በዩክሬን በሩሲያ በኩል ተሰልፈው ሲዋጉ የተገደሉ የ160 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ስም አረጋግጧል።















