ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚደክምዎ እና ሰውነትዎ ድንገት የሚዝል ከሆነ ኃይል ለማግኘት የሚረዱ 5 ቀላል መፍትሄዎች
ያለምክንያት ይደምዎታል? ሰውነትዎ ድንገት ይዝላል? እነዚህን 5 ቀላል የምግብ ለውጦችን ይሞክሩ።
አንዳንድ ሰው ቶሎ ይደክመኛል ይላል። አንዳንድ ሰው “ምግብ ስበላ ራሱ ይደክመኛል” ይላል። አንዳንዱ ደግሞ ቀኑን ገና ሳያጋምሰው “እንቅልፍ-እንቅልፍ ይለኛል” ይላል።
ይሄ ነገር ከተደጋገመ ቸል ማለት አያስፈልግም። የጤና ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። ሐኪም ማማካር ያስፈልጋል።
ኩንታል ሳንሸከም፣ ጋራ ሳንወጣ እንዲሁ ያለምክንያት ድካም እና መታከት ከተሰማን ምርታመነታቸውንን ይጎዳዋል። ትኩረት ማድረግ አንችልም።
ይህ ነገር ሌላ የጤና ችግር ሳይኖርብን የሚከሰት ከሆነ አንዳንዴ በአመጋገብ ሊቀየር ይችላል።
ሰማንታ ሄለር በኒውዯርክ ዩነቨርስቲ የሥነ ምግብ ተመራማሪ ናቸው።
ለዚህ የድካም እና የመዛል ስሜታችን የዘረመል አወቃቀራችን፣ በቀን የምናገኘው የእረፍት ጊዜ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ የማዘውተራችን ሁኔታ ወዘተ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም ምግብ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ይላሉ።
ደግሞም የምግብ ለውጥ ስናደርግ በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ መሆን አለበት ብለው ይመክራሉ።
“ከስኳር ራቁ አደራ’’ የሚሉት ተመራማሪው በየትኛውም መንገድ ስኳር ሰውነታችን ውስጥ ሲገባ፣ “መጀመሪያ ጉልበት ይሰጠናል፤ ከዚያ ግን ጉልበታችንን ይቀማናል፤ ስኳር አታላይ ነው” ብለዋል።
ጉልበታችን እንዳይዝል 5 የአመጋገብ ለውጦች
1. በርከት ያለ ውሃ ጠጡ
አንዳንዴ ድካም ምንጩ በቂ ፈሳሽ አለማግኘት ወይም በሰውነት ውስጥ ያለ ፈሳሽ መሟጠጥ ሊሆን ይችላል። ‘ዲሃይድሬሽን’ ይባላል በእንግሊዝኛው።
ብዙ ሰው ግን ድካሙን ለማጥፋት ቡና ይጠጣል። ወይም ጉልበት ሰጪ፣ ስኳር የተሞጀረባቸው፣ የኃይል መጠጦችን ይጎነጫል።
“እርግጥ ነው እነዚህን መጠጦች ስንጠጣ ለጊዜው ጉልበት ይሰጡናል። ነገር ግን ወዲያው ጉልበታችን ይዝላል” ይላሉ ባለሙያው።
አንዳንዴ ደግሞ የራበን ይመስለናል። ነገር ግን የሚያስፈልገን ተጨማሪ ምግብ ሳይሆን ውሃ ነው።
ሰውነታችን ውሃ ሲያጣ ጥማትን ከረሃብ ስሜት ጋር ያምታታል።
2. ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት አትዝለሉ
ብዙ ሰዎች ምግብ ዝለሉ እያሉ ይመክራሉ። ምግብ መዝለል የራሱ ጥቅም ሊኖረው ይችላል። የሚያመዝነው ግን ጉዳቱ ነው።
ምግብ መዝለል የጉሉኮስ መጠን እንዲወርድ ያደርጋል። ከዚያ ድካም ይሰማናል።
በቀን ውስጥ ሦስት ወሳኝ የምግብ ወቅትን የምትከተሉ ከሆነ ቁርስ፣ ምሳ እና እራትን አትዝለሉ። ትንንሽ አምስት የምግብ ጊዜ ካላችሁም ያን ተከተሉ።
ዋናው ነጥብ በሁለት የምግብ ክፍለ ጊዜዎች መካከል ረዥም ሰዓት አለማሳለፍ ነው።
“የጉሉኮስ መጠናችን በከፍተኛ መጠን እንዲጨምርም፣ እንዲቀንስም አያስፈለግም። አማካይ ሆኖ እንዲቀጥል ነው የሚፈለገው። ያ ሲሆን ጉልበታችን አይከዳንም” ይላሉ ተመራማሪው።
በእርግጥም ጥናቶች እንዳሳዩት ቁርስ የሚዘሉ ሰዎች ቁርስ ከማይዘሉት ሰዎች የበለጠበ ቀን ውስጥ በድምሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ካሎሪ ወደ ሰውነታቸው ያስገባሉ።
3. ቁርስ ላይ ፕሮቲን ተመገቡ
ፍራፍሬ ሁሌም ጥሩ ነው። በተለይ ጭማቂ ሳይሆን ፍራፍሬው ከነአሰሩ (ፋይበር) ብንበላው ጥሩ ነው።
ነገር ግን ጉልበት እንድናገኝ በፕሮቲን ቀኑን መጀመር አለብን ይላሉ ባለሙያዎች። ፕሮቲን ስንመገብ የመጥገብ እርካታ እናገኛለን። ያ ደግሞ ከመጠን ያለፈ ካሎሪ ወደ ሰውነታችን እንዳይገባ ያደርጋል።
ጥያቄው የትኛው ፕሮቲን ነው ጥሩ የሚለው ነው። ሥጋ ጥሩ የፕሮቲን ምንጭ ነው። ነገር ግን ብቸኛው አይደለም። ከጥራጥሬ፣ ከወተት ተዋጽኦ እና በተለይ ደግሞ ከቦሎቄ ልናገኘው እንችላለን።
ብዙዎቹ ጥራጥሬዎች ለምሳሌ በቂ አሰር አላቸው። ጉልበታችን እንዲጨምር የሚያደርግ በቂ ጉሉኮስም አላቸው።
አጃ ወይም ነጭ ካልሆነ እና ካልተፈተገ ስንዴ የተሠራ ዳቦ በርካታ ፋይበር ይገኝበታል። በሌላ ቋንቋ ‘ኮምፕሌክስ ካርቦሃይድሬት’ አገኘን ማለት ነው።
ኮምፕሌክስ ካርቦሃይድሬት ደግሞ ወደ ጥሩ ጉሉኮስ ይቀየር እና ጉልበት ይሰጠናል።
ተራ ካርቦሃይድሬቶች ግን ስታርች የሚባለው የስኳር ዓይነት ነው ያላቸው። አደጋቸው ታዲያ ቶሎ በሰውነታችን የደም መስመር ይገባሉ። ይህ ደግሞ የሰውነት የስኳር መጠናችን በአንድ ጊዜ ሰማይ እንዲነካ ያደርገዋል።
ይህ ለጤና ጥሩ አይደለም። እንዲህ ከሚያደርጉት መካከል ደግሞ በተለይ ነጭ የተፈተገ ፉርኖ ዳቦ እና ነጭ ሩዝ ይገኙበታል።
“ከተቻለ ሁሉም ሰው ቁርስ ላይ አነሰም በዛ ፕሮቲን ቢመገብ ነቃ ብሎ ያለድካም ቀኑን ያሳልፋል” ይላሉ ባለሙያው።
4. መክሰስ የሚበሉ ከሆነ ምረጡ
ብዙ ሰው መክሰስ ላይበላ ይችላል። በዋና ዋና ምግቦች መሀል አነስ ያለ ነገር ቀመስ ማድረግ ካስፈለገ ግን የሚመከሩ ምግቦች አሉ።
ቢቻል ቢቻል ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እና ለውዝ ይመከራሉ።
ለውዝ ብዙ ዓይነት አለ። ‘ዋልነት’ (Walnut) ለውዝ ለምሳሌ ከተገኘ ምርጥ ነው። ለልብ ጠቃሚ የሆነ ፋት አለው፤ ፋይበርም አለው፤ ቫይታሚን አለው። አይረንም (Iron) አለው። ድካምን ለመከላከል የሚያስችል ነገር በሙሉ የያዘ ነው።
ለመክሰስ ተመራጭ ነው ዋልነትስ ለውዝ።
5. የላመ እና የጣመ ነገር አስወግዱ
በመጨረሻም ድካም እንዳይሰማችሁ የተፈተጉ፣ የተራቆቱ፣ አሰር (fiber) የሌላቸው እህሎችን አስወግዱ።
ፉርኖ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ሩዝ ሊሆን ይችላል፤ ከተፈተገ ገብስ ወይም ስንዴ ከተሠራ ጥሩ አይደለም።
ከላመ እና ከጣመ እህሎች በኋላ ስኳር ተሞጅሮባቸው ሱፐርማርኬት ከተደረደሩ ማናቸውም የምግብ ዓይነቶች ራቁ።
ብዙዎቹ ከሱፐርማርኬት የሚገዙ የታሸጉ ምግቦች ከተፈተገ እህል ነው የሚመረቱት። ረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ደግሞ ኬሚካል ይጨመርባቸዋል። ስኳር ይሞጀርባቸዋል። ይህ ለጤና አደገኛ ከመሆኑም በላይ ድካም ያስከትልብናል።
ከዚህ አመጋገም ባሻገር የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት ጠቃሚ ነው ይላሉ ተመራማሪው።